Quantcast
Channel: ዜና
Viewing all 1779 articles
Browse latest View live

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ቀርባ ባልተከራከረችበት ክስ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባት

$
0
0
የቤጂንግ ኦሎምፒክ ድርብ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ

-    መጥሪያ በመኖሪያ ቤቷ ላይ ቢለጠፍላትም አለመቅረቧ ተገልጿል

የቤጂንግ ኦሎምፒክ ድርብ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የእሷ መሆኑ የተገለጸው የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪ፣ በተሳፋሪዎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት በማድረሱ ምክንያት በተመሠረተባት የፍትሐ ብሔር ክስ ቀርባ ባትከራከርም፣ በኦሮሚያ ክልል የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡

ክሱ የተመሠረተው በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ፣ በባለቤቷ አትሌት ስለሺ ስህንና በአሽከርካሪው አቶ ታምራት ቤኛ ላይ መሆኑን ፍርድ ቤቱ የሰጠው የውሳኔ ሰነድ ያስረዳል፡፡

ንብረትነቱ የአትሌት ጥሩነሽ መሆኑ የተገለጸው የሰሌዳ ቁጥሩ 3-15723 ኦሮ የሆነው የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ፣ ሰኔ 29 ቀን 2006 ዓ.ም. በዓል ለማክበር ከአሰላ ወደ ሸንኮራ ዮሐንስ በመሄድ ላይ እያለ፣ ሞጆ አካባቢ ሉሜ ወረዳ ዳንሳ ሹምቡሬ በሚባል ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ ተገልብጦ፣ በተሳፋሪዎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ማድረሱን የውሳኔው ሰነድ ያብራራል፡፡

በወቅቱ ተሳፍረው ከነበሩት ውስጥ ወ/ሮ አዱኛ ለሜቻ የተባሉ ግለሰብ የቀኝ ጆሮአቸው ሙሉ በሙሉ ሲቆረጥ፣ የግራ እጃቸው ሁለት ጣቶችም መቆረጣቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ የቀኝ እጃቸው ተሰብሮ ከጥቅም ውጪ መሆኑንና በአጠቃላይ በሕክምና የተረጋገጠ በአካላቸው ላይ 60 በመቶ ጉዳት እንደደረሰባቸው በአትሌቶቹና በሾፌራቸው ላይ የተመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡

ዕድሜያቸው 44 እንደሆነና ወደፊት 70 ዓመት እንደሚኖሩ የገለጹት ከሳሽ፣ ጤነኛ በነበሩበት ጊዜ በሚሠሩት ሥራ በቀን 150 ብር እንደሚያገኙ ጠቁመው፣ ለሕክምና ካወጡትና ወደፊት ሠርተው ከሚያገኙት ጋር ተደምሮ 1,554,000 ብር ካሳ እንዲከፈላቸው መጠየቃቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

የቀረበውን ክስ የተመለከተው የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ አትሌት ጥሩነሽና አትሌት ስለሺ ቀርበው እንዲከራከሩ የመጥሪያ ደብዳቤ በመኖሪያ ቤታቸው ላይ እንዲለጠፍ ትዕዛዝ ሰጥቶ የተለጠፈ ቢሆንም፣ አትሌቶቹ ሊቀርቡ አለመቻላቸውን ውሳኔው ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 70(ሀ) መሠረት አትሌቶቹ በሌሉበት ክርክሩ እንዲካሄድ በማዘዝ ክርክሩ ቀጥሏል፡፡

ሦስተኛ ተከሳሽ አሽከርካሪው አቶ ታምራት ቤኛ ተሽከርካሪው መገልበጡን፣ ነገር ግን ከአቅሙና ከሙያው በላይ በሆነ ምክንያት መሆኑን በመግለጽ ጉዳቱ መድረሱን ማረጋገጡን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አካቷል፡፡ ከሳሽ በአትሌቶቹ ላይ የሰዎች ማስረጃ እንዲያቀርቡ ታዘው፣ ያቀረቧቸው ምስክሮች ሾፌሩ ከአቅም በላይ በሆነ ፍጥነት ሲያሽከረክር በመገልበጡ፣ በከሳሽ ላይ የደረሰው ጉዳት ትክክል መሆኑን መመስከራቸውን አክሏል፡፡ የከሳሽን የቀን ገቢ በሚመለከት አንድ ምስክር 150 ብር ሲሉ ሌላኛው 100 ብር ማለታቸውን ለሕክምና፣ ለትራንስፖርትና ለቀለብ ገንዘብ ማውጣታቸንው መመስከራቸውን የውሳኔው ሰነድ ይገልጻል፡፡ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ሲመረምር ጉዳት መድረሱን ማረጋገጡን ጠቁሞ፣ ተሽከርካሪውም የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ መሆኑን ማረጋገጡንም አክሏል፡፡ በመሆኑም በ/ፍ/ብ/ሕ/ቁ 2018(1) መሠረት አትሌቷ ኃላፊነት ስላለባትና ንብረቱ የእሷ መሆኑ ስለተረጋገጠ፣ በከሳሽ ላይ ለደረሰው የአካል ጉዳት ኃላፊነት እንዳለባትም አስታውቋል፡፡

የከሳሽ የሰውነት ክፍሎች 60 በመቶ መጐዳታቸው በሕክምና ቦርድ መረጋገጡን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ በፍ/ሕ/ቁ/2012 መሠረት ተጐጂዋ በቀን 40 ብር ሊያገኙ እንደሚችሉ፣ በአገሪቱ ተጨባጥ ሁኔታ አንድ ሰው ሊኖር ይችላል ተብሎ የሚገመተው 55 ዓመት ስለሆነ ይኸው ተይዞ፣ በአጠቃላይ ከነወጪያቸው 128,520 ብር አትሌት ጥሩነሽ እንድትከፍል ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የወጪና ኪሳራ 2,000 ብርና የጠበቃ አበል አሥር በመቶ፣ እንዲሁም የዳኝነት እንድትከፍልም አክሏል፡፡ አትሌት ስለሺ የአትሌት ጥሩነሽ ባለቤት መሆኑ ከመገለጹ ባለፈ፣ አደጋ ያደረሰው ተሽከርካሪ ባለቤት ስለመሆኑ የቀረበበት ማስረጃ አለመኖሩን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ምንም ዓይነት ኃላፊነት እንደሌለበት አስታውቋል፡፡  


መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ 50 በመቶ እንደሚጨምር ይፋ አደረገ

$
0
0
መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ 50 በመቶ እንደሚጨምር ይፋ አደረገ

-ፋብሪካዎች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል

መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ከሚያወጣው ወጪ ባነሰ ታሪፍ እየደጎመ ሲያቀርብ መቆየቱን በመግለጽ፣ በአሁኑ ወቅት ቢያንስ ወጪውን የሚሸፍን ታሪፍ ማስከፈል በማስፈለጉ 50 በመቶና ከዚያም በላይ ሊደርስ የሚችል ጭማሪ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡ 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ እንዳስታወቁት፣ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት በድጎማ ሲያቀርበው የቆየው የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ በጣም ዝቅተኛ ነበር፡፡ ዝቅተኛ ብቻም ሳይሆን በአሁኑ ወቅት ኃይል አምርተው ለመንግሥት ለመሸጥ ፍላጎት ካላቸው ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ፣ የታሪፉ ዝቅተኛነት የድርድር አቅሙን እንዳዳከመበት አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት የታሪፍ ለውጥ የማድረግ አቋም እንዳለው፣ ዘ ኢኮኖሚስት ሰሞኑን በአዲስ አበባ ባካሄደው የኢትዮጵያ ጉባዔ ላይ ለታደሙ ኢንቨስትሮች ገልጸዋል፡፡ 

ኢንጂነር አዜብ እንዳብራሩት፣ መንግሥት በአሁኑ ወቅት አንድ ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ዘጠኝ የአሜሪካ ሳንቲም እያወጣ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ አንድ ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ስድስት የአሜሪካ ሳንቲም እያስከፈለ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የ50 በመቶና ከዚያም በላይ ለውጥ ሊሆን እንደሚችል ይፋ አድርገዋል፡፡ 

ኢንጂነሯ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ዝቅተኛ ነው ያሉት ታሪፍ በኃይል ማመንጨት ዘርፍ የሚፈለገውን ያህል የውጭ ኢንቨስትመንት እንዳይመጣ በማድረግ ሲጎዳው ቆይቷል፡፡ በመሆኑም የታሪፍ ለውጥ እንደሚደረግ በመገለጹ 14 ያህል የውጭ ኩባንያዎች ኃይል አመንጭተው ለመንግሥት ለማቅረብ ድርድር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ኩባንያዎች መካከል የአራት ቢሊዮን ዶላር የጂኦተርማል ኃይል ፕሮጀክት ይዞ የመጣው ሬይክቪክ ጂኦተርማል፣ ጄነራል ሞተርስና ብላክ ራይኖ የተሰኙት ይጠቀሳሉ፡፡ 

ብላክ ስቶን ለተባለው የአሜሪካ ኩባንያ እህት የሆነው ብላክ ራይኖ፣ በአሁኑ ወቅት ከጂቡቲ እስከ አዋሽ 550 ኪሎ ሜትር የሚዘረጋውን የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ይህ ኩባንያ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ስምምነት ከመድረሱም በተጨማሪ፣ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ወሳኝ ወደሆነው ምዕራፍ እንደሚሸጋገር ኩባንያውን በመወከል የተገኙት ሺሌሽ ሙራሊዳሃ አስታውቀዋል፡፡ እንዲሁም በኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ሥራ ላይ ለመግባት ፍላጎት እንዳለውም ለመንግሥት ማስታወቁን ኢንጂነር አዜብ ጠቁመዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል የታሪፍ ማሻሻያ እንደሚደረግ ይፋ መደረጉ ካስደነገጣቸው መካከል የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ጨርቃ ጨርቅና ጥጥ ኢንዱስትሪዎች ፌደሬሽን የቦርድ አባል አቶ ፋሲል ታደሰ አንዱ ናቸው፡፡ ኢንጂነር አዜብ የጠቀሱት የታሪፍ ጭማሪ ኢንዱስትሪዎችን ሳይሆን ኃይል ወደ ውጭ የሚልኩትን ኩባንያዎች የሚመለከት ነው በማለት ለመከራከር ቢሞክሩም፣ ጭማሪው ሁሉንም እንደሚመለከት ኢንጂነር አዜብ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ‹‹ይኼማ ሙቱ ማለት ነው፤›› ያሉት አቶ ፋሲል፣ የታሪፍ ጭማሪ ከዚህ ቀደም ተነስቶ አምራች ኢንዱስትሪዎችን እንደማይመለከት ከመንግሥት ጋር ስምምነት ተደርጎ እንደነበር በመግለጽ፣ የመረጃ ችግር እንዳይሆን በማለት ሥጋታቸውን ሲገልጹ ቢደመጡም፣ ኢንጂነሯ በድጋሚ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ሆኖም የታሪፉ ጭማሪ ሚዛናዊ እንዲሆን መደረጉን ኢንጂነር አዜብ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

ይሁንና ይጨመራል የተባለው ታሪፍ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ኢንጂነሯ ባይገልጹም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን ግን ተናግረዋል፡፡ 

ከሁለት ዓመት በፊት የአፍሪካ ልማት ባንክ በአፍሪካ በከፍተኛ ወጪ ኃይል የማመንጨት አዝማሚያዎችን የሚያስቃኘው ጽሑፍ ላይ እንዳሰፈረው፣ መንግሥታት ኃይል የማመንጨት አቅማቸው ደካማ እንዲሆን ከሚያደርጉ ፈተናዎች መካከል ከፍተኛ ወጪ አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥታት የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትን ለማሟላት በድጎማ ለማቅረብ መገደዳቸውን ባንኩ አስፍሯል፡፡ 

በሌላ በኩል መንግሥት በኢነርጂው መስክ ማስተካከል ይገባዋል ከተባሉት ችግሮች መካከል የውጭ ምንዛሪ ለውጥና ሊያስከትል የሚችለውን የኪሳራ ሥጋት እንዴት እንደሚመለከተው ተጠይቋል፡፡ የቢሮክራሲ ጣጣዎች፣ በጂኦተርማል መስክ የፋይናንስና የማበረታቻ ፓኬጆችን ማሻሻል እንዳለበት የሬይክቪክ ጂኦተርማልና የብላክ ራይኖ ኃላፊዎች መንግሥትን አሳስበዋል፡፡ 

 

የቀድሞ የአርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት በማታለል ወንጀል ተጠርጥረው ተከሰሱ

$
0
0
የቀድሞ የአርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት በማታለል ወንጀል ተጠርጥረው ተከሰሱ

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበሩት ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ፣ በማታለል ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡ 

ክሱ ቀደም ብሎ በ1998 ዓ.ም. ተመሥርቶባቸው የነበረ ቢሆንም፣ እንዲቋረጥ ተደርጎ ከቆየ በኋላ የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ በነበሩት አቶ ልዑል ወልዱ (አሁን የትግራይ  ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል) ትዕዛዝ ተቋርጦ የነበረው ክሱ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡

ተከሳሹ የተጠረጠሩበት የማታለል ወንጀል ‹‹አርበኛ ሳይሆኑ አርበኛ ነኝ›› በማለት፣ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የተሳሳተ መረጃና ማስረጃ አቅርበዋል የሚል መሆኑን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡ 

ተከሳሹ በ1938 ዓ.ም. ቢወለዱም በ1922 ዓ.ም. እንደተወለዱ፣ ጣሊያን ከ1928 ዓ.ም. እስከ 1933 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ መሳተፋቸውንና ‹‹አርበኛ ነኝ›› ማለታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ 

ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አርበኛ ሳይሆኑ እንደሆኑ በመግለጽና አሳሳች ነገሮችን በመናገር የራሳቸውን ማንነት መደበቃቸውን የሚገልጸው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ በ1937 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ ቁጥር 4/1937 አንቀጽ 33 ላይ በተደነገገው መሠረት አርበኝነታቸውን እንዳስመሰከሩ መናገራቸውንም ክሱ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ከግንቦት 25 ቀን 1993 ዓ.ም. እስከ 1994 ዓ.ም. ድረስ የኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የአንድ ሺሕ ብር ደመወዝተኛ ሆነው መሥራታቸውን ክሱ ይጠቁማል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ፕሬዚዳንት በመሆን 4,000 ብር ደመወዝና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እያገኙ በመሆኑ፣ በፈጸሙት የማታለል ወንጀል መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ኅዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መጥሪያ እንደተላከላቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

 

በነፃ ተሰናብተው ይግባኝ የተባለባቸው የፓርቲዎች አመራሮች በድጋሚ ተቀጠሩ

$
0
0

በሽብር ድርጊት ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ካቀረበባቸው በኋላ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ የተሰናበቱት የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣

ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ይግባኝ ተመርምሮ እንደሚያስቀርብና እንደማያስቀርብ ለመንገር በድጋሚ ተቀጠሩ

የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን በመቃወም የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ይግባኝ ተከትሎ ውሳኔው እንዳይፈጸም ዕግድ የሰጠው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. የውሳኔ መዝገቡን መርምሮ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ‹‹ያስቀርባል ወይም አያስቀርብም›› ብሎ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ የተቃወመው የሥር ፍርድ ቤት የውሳኔ መዝገብ እንዳልቀረበለት ገልጿል፡፡ በመሆኑም ውሳኔውና ዝርዝር ማስረጃዎቹ ተያይዘው እንዲቀርቡለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ 

በዕለቱ ይግባኝ የተጠየቀባቸው የአንድነት አመራር የነበሩት አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ አብረሃ ደስታና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ እንዲሁም አብረዋቸው ይግባኝ የተባለባቸው አቶ አብረሃም ሰለሞን በችሎት አልተገኙም፡፡ ፍርድ ቤቱ በችሎት በሰጠው ትዕዛዝ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

 

ትኩረት ባልሳበው የሊዝ ጨረታ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ከፍተኛ ዋጋ ቀረበ

$
0
0

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባወጣው 17ኛ የሊዝ ጨረታ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለአካባቢው ክብረወሰን የሆነ ዋጋ ቀረበ፡፡ ካለፈው ዓርብ ጥቅምት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እስከዚህ ሳምንት ሰኞና ማክሰኞ ባሉት ቀናት በተከፈተው 17ኛ የሊዝ ጨረታ፣ ከሌሎች ዙሮች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ተጫራች ናቸው የቀረቡት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከኃይሌ ጋርመንት ወደ ቱሉ ዲምቱ በሚወስደው መንገድ ላይ 12 ቦታዎች ለጨረታ አቅርቧል፡፡

በዚህ አካባቢ ለነዳጅ ማደያ ግንባታ የወጣው 8,127 ካሬ ሜትር 33,700 ብር በካሬ ሜትር የመጫረቻ ዋጋ ቀርቦለታል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የቀረበው የመጫረቻ ዋጋም በካሬ ሜትር 33,600 ብር ነው፡፡

በዚሁ አካባቢ ለቢዝነስ አገልግሎት ለወጣ 1,423 ካሬ ሜትር ቦታ በካሬ ሜትር 32,300 ብር የመጫረቻ ዋጋ ቀርቧል፡፡ ለዚህ ቦታ ሁለተኛ ተወዳዳሪ ሆኖ የቀረበው ተጫራች 18,235 ብር በካሬ ሜትር አቅርቧል፡፡

በዚህ አካባቢ ለቀረቡ ሌሎች ቦታዎች በካሬ ሜትር ከ12 ሺሕ ብር በላይ የመጫረቻ ዋጋ ቀርቧል፡፡ ይኼ የመጫረቻ ዋጋ ለአካባቢው ያልተለመደ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት በካሬ ሜትር ከሰባት ሺሕ ብር በላይ ቀርቦ እንደማያውቅ የአስተዳደሩ የሊዝ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር በዚህ 17ኛው ሊዝ ጨረታ ያቀረባቸው 110 ቦታዎች ሲሆኑ፣ ቦታዎቹ በሦስት ክፍላተ ከተሞች ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ለጨረታ የወጡት ቦታዎች ቁጥር አነስተኛ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ 1,500 ሰዎች ብቻ ናቸው የጨረታ ሰነድ የገዙት፡፡ ይህም ያልተለመደና ዙሩ የብዙዎችን ትኩረት ያልሳበ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍላተ ከተማ በተጨማሪ በአቃቂና በየካ ክፍላተ ከተሞች በቅደም ተከተል 52 እና 46 ቦታዎች ለጨረታ ቀርበው ነበር፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከቀረቡት ቦታዎች ውስጥ ስምንቱ ተጫራች ሲያጡ፣ ቀሪዎቹ ቦታዎች ከአራት ሺሕ እስከ 13 ሺሕ ብር ድረስ በካሬ ሜትር የመጫረቻ ዋጋ ቀርቦላቸዋል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ፈረንሣይ ለጋሲዮን አካባቢ 21 ቦታዎች ለጨረታ ሲቀርቡ፣ የተቀሩት ቦታዎች አያት አካባቢ የወጡ ናቸው፡፡ በአያት አካባቢ አብዛኛዎቹ ቦታዎች በካሬ ሜትር ከ20 ሺሕ እስከ 22 ሺሕ ብር ድረስ የመጫረቻ ዋጋ ቀርቦላቸዋል፡፡

በአንፃሩ የ17ኛው ዙር ዝቅተኛ የመጫረቻ ዋጋ በፈረንሣይ ለጋሲዮን አካባቢ ለቀረበ ቦታ የተሰጠው ነው፡፡ በዚህ አካባቢ 286 ካሬ ሜትር ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ጨረታ የቀረበ ሲሆን፣ ለዚህ ቦታ ሁሴን ዓባይ የተባሉ ተጫራች በካሬ ሜትር 3,777 ብር አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሊዝ ሥሪት ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ ከዚህ ዙር ቀደም ብሎ የወጡት ቦታዎች በሙሉ ውድ ዋጋ ሲቀርብላቸው የቆየ ከመሆኑ አንፃር፣ 17ኛው ዙር ብዙ ተጫራች አልቀረበለትም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለጨረታ የቀረቡ ቦታዎች ቁጥርም አነስተኛ በመሆኑ፣ የብዙዎችን ትኩረት አልሳበም በማለት ባለሙያዎቹ አስረድተዋል፡፡ 

 

 

የልጃቸውን ጓደኛ በመግደል የተጠረጠሩት ሐኪም ታሰሩ

$
0
0

ጥቅምት 20 ለ21 አጥቢያ 2008 ዓ.ም. የልጃቸውን ጓደኛ በሽጉጥ ተኩሰው በመግደል የተጠረጠሩ ሐኪም፣ ከነመሣሪያቸው በቁጥጥር ሥር ውለው እየተመረመሩ መሆኑ ታወቀ፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 13/14 ልዩ ሥፍራው ማጂክ ካርፔት በሚባለው ትምህር ቤት አካባቢ የተገደለው ወጣት ቴዎድሮስ ሲሳይ ይባላል፡፡

ቴዎድሮስ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በዕለቱ የማንቸስተር ዩናይትድ ግጥሚያ ሲመለከቱ አምሽተው በዚያው ሲዝናኑ ያመሻሉ፡፡ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት አካባቢ ሟች ቴዎድሮስና ጓደኞቹ በግድያ ወደተጠረጠሩት ዶ/ር ተስፋዬ ያዕቆብ (በሰላም ከፍተኛ የጥርስ ክሊኒክ የጥርስ ሐኪም ናቸው ተብሏል) ቤት መሄዳቸውን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡

የተጠርጣሪው ልጅ መጠጥ ሲቀምስ የመጮህና የመበጥበጥ ባህሪ እንዳለበት የሚናገሩት የዓይን እማኞች፣ ጓደኞቹን ይዞ ቤቱ እንደደረሰ ባህሪው በመነሳቱ ሟችና ሌሎች ሁለት ጓደኞቹ ከግቢ ወጥተው በመሄድ ላይ እያሉ ተጠርጣሪው ሽጉጥ ይዘው መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ አንደኛው ወጣት ኳስ ሲያዩ ማምሸታቸውን በማስረዳት ላይ እያለ ተጠርጣሪው ወደ ሟች ተጠግተው በመተኮስ እንደገደሉት የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

የሟች ጓደኞች ተጠርጣሪው ሐኪም ሆን ብለው እንደገደሉት የገለጹ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪው ግን ባርቆባቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤት ማስረዳታቸውን ሪፖርተር ከፖሊስ ያገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪውን ሐኪም በቁጥጥር ሥር አድርጎ በመመርመር ላይ የሚገኘው ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት አቅርቦ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል፡፡ ሟች ቴዎድሮስ ሲሳይ በሳሪስ አቦዬ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀኑ ስምንት ሰዓት የቀብር ሥርዓቱ መፈጸሙም ታውቋል፡፡

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 1,600 አመራሮች ሾመ

$
0
0

-በዚህ ሳምንት በማዕከል የሚደረገው ለውጥ ይፋ ይሆናል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለክፍላተ ከተማና ለወረዳዎች 1,600 አመራሮችን ሾመ፡፡ ለተሿሚዎቹ ባለፈው ሳምንት ለሦስት ቀናት የቆየ የፖሊሲ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሙስናና በብልሹ አሠራር ገምግሞ ካሰናበታቸው አመራሮች በተጨማሪ፣ ከዲፕሎማ በታች የትምህርት ደረጃ ያላቸውን አመራሮች አንስቷል፡፡ በእነዚህ ተሿሚዎች ምትክ ለአሥሩ ክፍላተ ከተሞችና ለ116 ወረዳዎች የተሾሙት 1,600 አመራሮች ከመጀመሪያ ዲግሪና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ናቸው ተብሏል፡፡ 

እነዚህ ተሿሚዎች አዳዲስና ከዚህ ቀደም በአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች በተለያዩ ደረጃዎች ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ተሿሚዎች ባለፈው ሳምንት ከማክሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት የቆየ የፖሊሲ ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡ 

የፖሊስ ማብራሪያውን የሰጡት የአዲስ አበባ አቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ይስሐቅ ግርማይና የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተወልደ ገብረ ፃድቃን ናቸው፡፡ 

በፖሊሲ ማብራሪያው እነዚህ ተሿሚዎች በከተማው መልካም አስተዳደር ማስፈን፣ የፀረ ሙስና ትግል በብቃት ማካሄድ እንዳለባቸውና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት መሥራት እንደሚኖርባቸው፣ በፖሊሲ ማብራሪያው ማሳሰቢያ እንደተሰጣቸው ከአቅም ግንባታ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተለይ አቶ ይስሐቅ በሥልጠና ወቅት እንደተናገሩት፣ ከዲፕሎማ በታች የትምህርት ደረጃ ያላቸው ከኃላፊነት የተነሱ አመራሮች በቀጣይ ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበት አሠራር ይፈጠራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተነሱት የቀድሞ አመራሮች በጥቃቅንና በአነስተኛ ማኅበራት ተደራጅተው የተለያዩ ሥራዎችን እንዲያካሂዱ ይደረጋል ሲሉ አቶ ይስሐቅ በሥልጠናው ወቅት መግለጻቸው ታውቋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በክፍላተ ከተሞችና በወረዳዎች ሲያካሂድ የቆየውን ሹም ሽር በማጠናቀቅ፣ ትኩረቱን በማዕከል ደረጃ በሚያካሂደው ለውጥ ላይ አድርጓል፡፡ በዚህ ሳምንት መጨረሻ በማዕከል ደረጃ የሚያካሂደውን የመዋቅርና የባለሥልጣናት ሹም ሽር ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡      

 

የገቢዎችና ጉምሩክ ከፍተኛ ኦዲተርና ኦፊሰሮች በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰሱ

$
0
0

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የመርካቶ ቁጥር ሁለት ቅርንጫፍ ከፍተኛ ኦዲተርና ሦስት ኦፊሰሮች ጉቦ በመቀበል ከባድ የሙስና ወንጀል ጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ተከሰሱ፡፡

ተከሳሾቹ የግል ተበዳይ አቶ ዮሐንስ ጥጋቡ የተባሉትን በጨርቃ ጨርቅ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴ፣ ‹‹ግዢና ሽያጭ አልተጣጣመም፣ በቆጠራ የሚፈጠረውን ጉድለት ባላንስ እናደርግልዎታለን፤›› በማለት ሁለት ሚሊዮን ብር ጉቦ መጠየቃቸውን፣ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡

የጉቦ መቀበል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኞች አቶ መሠረት ታደሰ የተባባሪዎች ምልመላና ሥልጠና ኦፊሰር፣ አቶ አበበ ደቦ ቡልቱሜ የኢንቬስትጌሺን ከፍተኛ ኦዲተር፣ አቶ አያና ጋሩማ የኢንተለጀንስ አሰባሰብ ጀማሪ ኦፊሰር፣ አቶ ሀብታሙ ታደሰ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምቦ ቅርንጫፍ ኦፊሰርና አቶ አብዲሳ ደቦ ቡልቱሜ የባንኩ የሰው ኃይል አስተዳዳር ባለሙያ ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ ከላይ የተጠቀሰውን ሁለት ሚሊዮን ብር ጉቦ የጠየቋቸው አቶ ዮሐንስ ባለመስማማታቸው፣ አንደኛ ተከሳሽ አቶ መሠረት አደራዳሪ መስሎ ነጋዴውን በመቅረብ፣ ‹‹ኦዲተሮቹ ብዙ ገንዘብ መቀበል ስለለመዱ አንተ ሁለት መቶ ሺሕ ብር ብትሰጣቸው ምንም አይደለም፤›› ቢላቸውም ተበዳዩ አለመስማማታቸውን ክሱ ይጠቁማል፡፡ 

የነጋዴውን አለመስማማት የተረዱት ተከሳሾች ያላቸውን ዕቃ ብዛት በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋቸው እንደሰጧቸው የሚገልጸው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ በዝርዝር የሰጡት ዕቃ ጉድለት እንደሚያመጣና ጠቅላላ የዕቃውን ብዛት እንዳልሰጧቸው ሲገልጹላቸው፣ ተበዳዩም ካልተቆጠረ እንደማይታወቅ በመግለጽ እንደተከራከሯቸው ክሱ ያስረዳል፡፡

የግል ተበዳዩን በተለያየ መንገድ ስላስጨነቋቸው ግንቦት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ለአንደኛ ተከሳሽ አራት መቶ ሺሕ ብር መስጠታቸውን፣ በድጋሚ በተለያዩ ቀናት በድምሩ ሁለት መቶ ሺሕ ብር መስጠታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ተከሳሾቹ ሰነዱን ሲመረምሩ ተበዳዩ 12 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ከፍተኛ ዕዳ እንደሚመጣባቸው ማወቃቸውን በመንገር፣ ተበዳዩን በማስጨነቅ አራት መቶ ሺሕ ብር እንዲሰጧቸው ማድረጋቸውን፣ በአጠቃላይ በተለያዩ ቦታዎች በመቅጠር ተከሳሾች ከተበዳይ 1.2 ሚሊዮን ብር መቀበላቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

አቶ መሠረት የተባለው ተከሳሽ ጉቦ በመቀበል ያገኘውን ገንዘብ ለመሰወርና ለመደበቅ፣ አምቦ ከተማ ለሚኖረውና ለአራተኛ ተከሳሽ ወንድሙ አቶ ሀብታሙ አምስት መቶ ሺሕ ብር መስጠቱ በክሱ ተጠቅሷል፡፡ አቶ ሀብታሙ የገንዘቡ አመጣጥ ሕገወጥ መሆኑን እያወቀ፣ አምቦ ከተማ ቀበሌ 02 ውስጥ ስፋቱ 200 ካሬ ሜትር ቦታ በ140 ሺሕ ብር በእናቱ ስም እንደገዛለት፣ 100 ሺሕ ብር ደግሞ ለሌላ ግለሰብ እንዲያስቀምጥለት መስጠቱን ክሱ ያብራራል፡፡ አቶ አበበ ደግሞ ለአቶ አብዲሳ 287,900 ብር ሲሰጠው ገንዘቡን መሬት ውስጥ መቅበሩን፣ አቶ አያና የተባለው ሦስተኛ ተከሳሽ ደግሞ በአምቦ ከተማ 400 ካሬ ሜትር መሬት በ80 ሺሕ ብር በመግዛት በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ለማሰመሰል መሥራታቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ፈጽመዋል በተባለው ጉቦ መቀበል ከባድ የሙስና ወንጀልና በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሙስና ወንጀል የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡

     

 

አይኤምኤፍ ለመንግሥት ያቀረባቸውን የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ይፋ አደረገ

$
0
0
አይኤምኤፍ ለመንግሥት ያቀረባቸውን የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ይፋ አደረገ

-በግል ባንኮች ላይ የተጣለው የቦንድ ግዥ እንዲነሳ ጠይቋል

-የታክስ ነፃ መብቶች እንዳይሰጡ ብሏል

-የብር የመግዛት አቅም መቀነስ አለበት ብሏል

የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ከገመገመ በኋላ፣ ለመንግሥት ያቀረባቸውን የፖሊሲ ማሻሻያ ምክረ ሐሳቦች ይፋ አደረገ፡፡

በሚስ አንድሪያ ሪቸር ሁም የተመራው ስድስት አባላት ያሉት የአይኤምኤፍ ቡድን በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በመገኘት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አህመድ፣ ከብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ነዋይ ገብረ አብ ጋር በአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎችና መወሰድ ስላለባቸው የጥንቃቄ ፖሊሲ ዕርምጃዎች መወያየታቸውን፣ ባለፈው ዓርብ ጥቅምት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው የውይይቱ አጠቃላይ ይዘት መግለጫው ይፋ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ በተለይ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ እንደምትገኝና በእነዚህም ጊዜያት ውስጥ የአገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ እያደገ መምጣቱን፣ የአገሪቱ የድህነት ደረጃም በ2002 ዓ.ም. ወደ 29.6 በመቶ መውረዱን ይገልጻል፡፡ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ያለውን የድህነት መጠን ሪፖርት አላመለከተም፡፡

በ2007 ዓ.ም. የአገሪቱ ዕድገት ካለፉት ዓመታት ቀዝቀዝ ቢልም 8.7 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይገልጻል፡፡ የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ የተረጋጋ እንደሆነ የሚገልጸው የአይኤምኤፍ ዝርዝር መግለጫ፣ ይህንን መረጋጋት የሚረብሹ ግፊቶች እያንዣበቡ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ከእነዚህም መካከል ወደ ባለሁለት አኃዝ የተሸጋገረው የዋጋ ግሽበት፣ የብር የመግዛት አቅም አሁንም ከፍተኛ በመሆኑ መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማምጣት አስቸጋሪ መሆኑ፣ የመንግሥት ከፍተኛ ኢንቨስትመንትና የውጭ ብድር ጫና እየገዘፉ መምጣታቸውን ይገልጻል፡፡

የአይኤምኤፍ ቡድን ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በአራት መሠረታዊ ነጥቦች ላይ ተወያይቶ ምክረ ሐሳቡን መለገሱን፣ ዝርዝር የውይይቱ መግለጫው ያስረዳል፡፡ 

የመጀመሪያው የመወያያ ነጥብ የተረጋጋውን ማክሮ ኢኮኖሚ መጠበቅ ሲሆን፣ እያሻቀበ የሚገኘው የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ዕዳ ክምችት፣ የመንግሥት ከፍተኛ ኢንቨስትመንትና የብር ምንዛሪ ማነስ ማክሮ ኢኮኖሚውን ሊያዛቡት ይችላሉ ብሏል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ኢንቨስትመንቱን የተመጠነ እንዲያደርግ፣ የዋጋ ንረቱን ለመከላከል ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት በጀት ጉድለት መሙያ የሚያበድረውን እንዲያቆም ሲል አሳስቧል፡፡

ሁለተኛው የመወያያ ነጥብ ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭን መፍጠር መሆኑን የሚገልጸው መረጃው፣ የአገር ውስጥ ቁጠባ እያደገ ቢመጣም መንግሥት እንዳቀደው ቁጠባውን የአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርቱን (GDP) 40 በመቶ ለማዳረስ ቢሆንም፣ ገና በዚህ ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡

በመሆኑም መንግሥት የታክስ መሠረቱን እንዲያሰፋና የፋይናንስ ተቋማት የረዥም ጊዜ ብድር ላይ እንዲያተኩሩ ጠይቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ለኢንቨስተሮች የሚሰጠውን የታክስ ነፃ ዕድል በማስቀረት የኢንዱስትሪ ዞን መሠረተ ልማቶችን እንዲያስፋፋ ምክረ ሐሳቡን ለግሷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መንግሥት በታክስ ነፃ ማበረታቻ በየዓመቱ የአገሪቱን አጠቃላይ ምርት ሦስት በመቶ እያጣ በመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም በአገሪቱ የግል ንግድ ባንኮች ላይ የተጣለው የ27 በመቶ ቦንድ ግዥ ግዴታ እንዲነሳ፣ ባንኮችም ይህንን ገንዘብ ለብድር እንዲያውሉት ቢደረግ የሚል ሐሳቡን አቅርቧል፡፡

ሦስተኛው የመወያያ ነጥብ የነበረው የውጭ ገበያ ውድድርን ማሳደግና የውጭ ተፅዕኖን መቀነስ ናቸው፡፡ በዚህ ነጥብ ሥርም ኤክስፖርት ላይ ያተኮረ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ለመጀመር የሚፈጀውን የጊዜና የወጪ ፍጆታ መቀነስ፣ የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድርን መጨረስና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት መያዝ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

በአራተኛው የውይይት ነጥብ ዕድገቱ የተመጣጠነ እንዲሆንና በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ ውጤቱ የሚታይ ዕድገት መፍጠር አስፈላጊነትን፣ አይኤምኤፍ በውይይቱ ወቅት ማንሳቱን አስታውቋል፡፡

መንግሥት በበኩሉ ጥብቅ የሆነ የገንዘብ ፖሊሲ በመከተል ማክሮ ኢኮኖሚው እንደተረጋጋ እንዲቆይ እንደሚያደርግ፣ መሠረታዊ የፍጆታ ምግቦችን በማቅረብ የዋጋ ግሽበት አደጋን መቅረፍ እንደሚቻል፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት በጀት ጉድለት የሚሰጠው ብድር እንዲቀንስ እንደሚደረግ መግለጹ ተመልክቷል፡፡

ከዚህ ውጭ የቀረበው ሥጋት ማለትም የውጭ ዕዳ ጫና የሚለው የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚያሠጋ አለመሆኑን መንግሥት ማስታወቁን፣ ለዚህ የሚሰጠው ምክንያት ደግሞ የሚወስደው የውጭ ብድር የሚውለው መልሶ መክፈል ለሚያስችሉ ፕሮጀክቶች መሆኑን በመግለጽ መቃወሙን የውይይቱ ዝርዝር መግለጫ ያስረዳል፡፡ የብር የመግዛት አቅም ከፍተኛ መሆን የሚፈጥረው ችግር መኖሩን መንግሥት እንደሚረዳ፣ ነገር ግን የመግዛት አቅሙን ማሳነስ የመንግሥት የውጭ ብድርን ከፍ እንደሚያደርገው በመግለጽ በተጠና ሁኔታ የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ እንደሚደረግ መግለጹም ተወስቷል፡፡

ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ መፍጠርን አስመልክቶ የአይኤምኤፍ ቡድን ያቀረበውን የታክስ መሠረት ማስፋት መንግሥት እንደሚቀበለው፣ ነገር ግን በባንኮች ላይ የተጣለውን የ27 በመቶ ቦንድ ግዥ ለማንሳት እንደማይፈልግ ገልጿል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ይህንን ግዴታ ከባንኮች ላይ ቢነሳም፣ ባንኮቹ ይህንን የገንዘብ መጠን ለብድር ያውሉታል የሚል እምነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡ ለኢንቨስተሮች የሚሰጠው የታክስ ነፃ ማበረታቻንም እንደማያነሳ፣ ነገር ግን ቁጥጥር እንደሚያደርግ መግለጹ ታትቷል፡፡

 

በድርቅ በተጠቁ የአማራ ክልል አካባቢዎች የውኃ ወለድ በሽታዎች ሥጋት ተፈጠረ

$
0
0

በአማራ ክልላዊ መንግሥት በድርቅ በተጠቁ በተለያዩ ዞኖች የተከለሉ ውኃ ምንጮች ውስንነት፣ ከንፅህና ጋር ለተያያዙ በሽታዎች መፈጠር ምክንያት መሆኑ ተገለጸ፡፡ 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በዚህ ሳምንት በወጣው ሪፖርት፣ ‹‹ስካቢስ›› የተሰኘ ወረርሽኝ በምሥራቅ ጎጃም፣ በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ወሎና በዋግ ህምራ ዞኖች በሚገኙ 20 ወረዳዎች መከሰቱን አስታውቋል፡፡ በዋግ ህምራ ዞን ብቻ 88,905 ግለሰቦች በወረርሽኙ መያዛቸው ታውቋል፡፡ የጤና ጥበቃ  ሚኒስቴር በበሽታው ለተጠቁ ሥፍራዎች መድኃኒቶችን በመላክ ላይ መሆኑን የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ የችግሩ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ የተለያዩ ዘርፎችን ትብብር የሚጠይቅ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ 

በሽታው ተዛማች በመሆኑ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የተጀመረው ጥረት በአፋጣኝ ተስፋፍቶ መቀጠል እንደሚኖርበት የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ ወረርሽኙ የተከሰተው ከድርቁ ጋር ተያይዞ እንደሆነ በሪፖርቱ አስፍሯል፡፡ 

ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ የምግብ ፕሮግራም የሚያስፈልጋቸው ሕፃናት ቁጥር ከሌላው ጊዜ በ20 በመቶ መጨመሩን፣ የተጎጂዎቹ ቁጥር በየወሩ እየጨመረ መሄዱን ጽሕፈት ቤቱ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በመስከረም ወር የተመዘገቡ በምግብ ዕጦት የተጎዱ ሕፃናት ቁጥር 35,216 የነበረ ሲሆን፣ በነሐሴ ወር ከተመዘገቡት 43,391 ሕፃናት የ19 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ቢሆንም፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በመስከረም ወር የተመዘገበው በምግብ ዕጦት የተጎዱ ሕፃናት ቁጥር ከሌላው ማንኛውም ዓመት የ20 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ 

ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበው በአማራ ክልል እንደሆነ የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ በየወሩ በክልሉ 6,489 በምግብ ዕጦት የተጎዱ ሕፃናት ወደ ምግብ ፕሮግራም እንደሚገቡ ጠቁሟል፡፡ 

በኤልኒኖ ምክንያት በተፈጠረው አየር መዛባት የተከሰተው ድርቅ እየተባባሰ መምጣቱን ጠቅሶ፣ እየጨመረ የመጣውን የምግብ ዕርዳታ ፍላጎት መጠን ለማሟላት የኢትዮጵያ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርብም አጥጋቢ ምላሽ አለመገኘቱን አስታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ. የ2015 እና የ2016 የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል የገንዘብ ምንጭ አለመኖሩ አሳሳቢ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ እ.ኤ.አ. ለ2016 የሚያስፈልገው ዕርዳታ በአስቸኳይ መገኘት እንዳለበት የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ ዕርዳታውን አጓጉዞ ከሚፈለገው ሥፍራ ለማድረስ ከሦስት እስከ አምስት ወራት ቀድሞ መዘጋጀት እንደሚኖርበት ጠቁሟል፡፡ 

መንግሥት ከለጋሾች የሚፈለገውን ያህል የገንዘብ ድጋፍ ባለማግኘቱ ሁኔታዎች በከፉበት አካባቢ በራሱ ወጪ ዕለታዊ ዕርዳታዎች በማድረግ ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ 

ከመንግሥት የመጠባበቂያ ምግብ ክምችት 50,000 ሜትሪክ ቶን ስንዴና 300 ሜትሪክ ቶን የምግብ ዘይት በመከፋፈል ላይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የከብቶች መኖ በመታደል ላይ መሆኑን፣ የውኃ ጉድጓዶች ጥገና ሥራ እየተከናወነ እንደሆነና የውኃ ማጣሪያ ኬሚካሎች በመሠራጨት ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት በተፈጠረው ድርቅ ምክንያት 8.2 ሚሊዮን ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ የዕርዳታ አቅርቦቱ ካልተፋጠነና የአየር ፀባዩ ካልተለወጠ የተረጂዎች ቁጥር በሁለት ወራት ውስጥ 15 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ 

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወሳኝነታቸውን ያሳዩበት መድረክ

$
0
0
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወሳኝነታቸውን ያሳዩበት መድረክ

በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እስከዛሬ ሲደረጉ ከነበሩ ከንግግር ያልዘለሉ የቁርጠኝነት ማሳያዎች አንድ እርከን የዘለለ እንደሆነ የተነገረለት በጥናት ላይ የተመሠረተ ውይይት፣ በቅርቡ በመንግሥት ከፍተኛው አስፈጻሚ አካል ተካሂዷል፡፡

ይህ ለሕዝብ ከወትሮው በተለየ በከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል ወቀሳና ተጠያቂነትን ያስነሳው ውይይት፣ መነሻ ምክንያቱ ታች መሬት ተወርዶ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ የዳሰሳ ጥናት መካሄዱ ነው፡፡ የጥናቱ አቅራቢዎች በውይይቱ ወቅት የችግሩን ስፋትና መጠን ሲያስረዱ፣ ለወትሮው የሐሳብ ልዩነቶቻቸውን ከመጋረጃ በስተጀርባ በመጨረስ ለሕዝብ አንድ ሆነው በመቅረብ የሚታወቁት የኢሕአዴግ ቱባ ባለሥልጣናት፣ በአደባባይ ልዩነቶቻቸውን በግልጽ ያወጡበት ውይይት እንደነበር ታይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአገሪቱ ቁንጮ ባለሥልጣን ሆነው ከመጡበት ጊዜ  ጀምሮ፣ በግልጽ የሥልጣን ባለቤትና የገዥው ፓርቲ አቅጣጫ የመወሰን ሥልጣን እንዳላቸው ያሳዩበትም ነበር፡፡ በተለይ በመሬት፣ በኢንቨስትመንት፣ በፍትሕና በተለያዩ መስኮች በጥናቱ የቀረበው አሳሳቢ ሥጋት ካልተወገደ አደገኛነቱንም በማስጠንቀቅ አውስተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንኦት በመስጠት ለአገሪቱም ሆነ ለሕዝቡ አደገኛ የሆነውን የመልካም አስተዳደር ችግር መታገል የሕዝብ አመኔታን እንደሚያስገኝ አስታውቀው፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትም በውስጣቸው መደንገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ከውይይቱ በኋላ ባለሥልጣናት በብሔር፣ በዝምድና፣ በጥቅማ ጥቅምና በመሳሰሉት ከተሳሰሯቸው ኔትወርኮቻቸው እንዲላቀቁም አስጠንቅቀዋል፡፡ ዝርዝሩን ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ ወይም በ ፖለቲካ ገጽ ይመልከቱ፡፡

 

አዲሱ ምደባ ሒልተን ሆቴልን ወደ ሦስት ኮከብ ዝቅ አደረገው

ለካቢኔው ሐሰተኛ ሰነድ ቀርቦ በይዞታቸው ላይ ውሳኔ የተላለፈባቸው አቤቱታ አቀረቡ

$
0
0

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በመልሶ ማልማት ይዞታቸውንና አካባቢያቸውን ለሚለቁና ለሚያለሙ ነዋሪዎች ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት፣ ለልማቱ ሲሉ እንደሚለቁ መስማማታቸውን በሚገልጽ ሐሰተኛ ደብዳቤ፣ ከሕግ አግባብ ውጪ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው የሚናገሩ ባለይዞታዎች አቤት እያሉ ነው፡፡ 

 

ከወረዳ እስከ ከተማ አስተዳደር ድረስ ፍትሕ ለማግኘት እየሮጡ መሆናቸውን የሚናገሩት እነዘለቃ በቀለ፣ ፈትያ እስማኤልና ጀማል አብዶ የሚባሉ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 የፌዴራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር መዳረሻ አካባቢ የሚገኙ ባለይዞታዎች ናቸው፡፡ አስተዳደሩ ያወጣውን መመርያ ተከትለው ባላቸው ቅድሚያ የማልማት መብት እንዲያለሙ ጥያቄ ያቀረቡት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ሕጋዊ የሆነውን ይዞታቸውን ለማልማት አቅም እንዳላቸው በመግለጽ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመልሶ ማልማት ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ‹‹የአስተዳደሩ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቦርድ የካቲት 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ቦታው ለባለሀብት ተሰጥቷል፤›› የሚል ምላሽ ሰኔ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

አቤት ባዮቹ እነሱ የማልማት ጥያቄ ሲያቀርቡ ሊዝ ቦርድ ውሳኔ እንደሰጠ ቢነገራቸውም፣ ቦርዱ በተሰበሰበበት ወቅት ካሉት ዘጠኝ አባላት ከንቲባውን ጨምሮ አምስት አባላት ባለመገኘታቸው ውሳኔው ፈራሽ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ባለይዞታዎቹ ድጋሚ ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት ቦርዱ በሊዝ አዋጅ ተተክቶ የፈረሰ ቢሆንም፣ የመልሶ ማልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት የአስተዳደሩ ሊዝ ቦርድ መፍረሱን ስለማያውቅ የሚሰጣቸው ምላሽ በወቅቱ ካለው ሁኔታ ጋር አልተጣጣመላቸውም፡፡ አቤቱታቸውን ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ቢያቀርቡም፣ ቦታው በአካባቢ ልማት ዕቅድ ተጠንቶ የተከለለ በመሆኑ እንደማያስተናግዳቸው እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል፡፡ 

ሕግ በሚፈቅድላቸው መንገድ የማልማት መብታቸው እንዲፈቀድላቸው ለከተማው ከንቲባ ታኅሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡ 1,500 ካሬ ሜትር በሆነ ቦታቸው ላይ ለማልማት ክፍለ ከተማውን የፕላን ስምምነት ሲጠይቁ ቦታው ለሌላ ግለሰብ መሰጠቱን፣ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ደግሞ በለገሀር ጥናት 40 ሔክታር ለመልሶ ማልማት መያዙን በመንገር፣ የተለያዩ ምላሾችን በመስጠት በደል እየደረሰባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በሊዝ ቦርድ ውሳኔ መሠረት ቦታው ለኢንቨስተር እንደተሰጠ የተገለጸላቸው ቢሆንም፣ ሊዝ ቦርድ (የሊዝ አዋጅ በ2004 ዓ.ም. ሲወጣ ፈርሷል) በወቅቱ ከነበሩት ዘጠኝ አባላት ውስጥ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳን ጨምሮ አምስት አባላት ባልተገኙበትና ኮረም ሳይሞላ ተወስኗል መባሉ፣ ምን ያህል በደል እየደረሰባቸው እንደሚገኝ እንደሚያሳይ ለከንቲባ ድሪባ የጻፉት ደብዳቤ ያስረዳል፡፡

ለከንቲባ ድሪባ ኩማ የጻፉትን ደብዳቤ ተንተርሶ የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ኮሚቴ በመዋቀር ባደረገው ጥናት፣ ተበዳዮች እየደረሰባቸው ያለው በደል እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ድምዳሜ ላይ ደርሶ ውሳኔ ለማሰጠት፣ በአጀንዳ ቁጥር 5 ‹‹የእነዘለቃ በቀለ፣ ፈትያ እስማኤል ኢብራሂምና ጀማል አብዶ ጉዳይ›› ተብሎ ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ ውስጥ፣ በአንድ አንቀጽ ተበዳይ ነን የሚሉትና የማልማት አቅም እንዳላቸው እየተከራከሩ የሚገኙት ተበዳዮች ‹‹ልማቱን ማደናቀፍ አንፈልግም፡፡ ጥያቄያችንን አንስተናል፡፡ ልማቱ አይታነቅ፡፡ ሊዝ ቦርድ በወሰነው መሠረት ለኢንቨስተሩ ይወሰንላቸው፤›› ብለው እንደተስማሙና በፊርማቸው ያረጋገጡ በማስመሰል ሐሰተኛ ሰነድ አያይዘው ለአስተዳደሩ ማቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡ 

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ባደረገው ስምንተኛው የመሬት ሊዝ ጉዳይ ስብሰባ፣ የቀረበለትን ሐሰተኛ ሰነድ መመርመር ሳያስፈልገው ማፅደቁን ባለይዞታዎቹ አብራርተዋል፡፡ ጉዳዩ ገና ከጅምሩ በተለያዩ ክፍሎች በሚሠሩ ኃላፊዎች እየተደናቀፈባቸው መሆኑን ያስተዋሉት ባለይዞታዎቹ፣ ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዝርዝር መረጃ በማካተት ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ያሳወቁ ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ እስካሁን ምንም እንዳላለ ተናግረዋል፡፡ ይኼ ሁሉ ነገር የተካሄደው ተበዳዮች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው እየታየ ባለበት ጊዜ መሆኑን ገልጸው፣ ፍርድ ቤቱ ኃላፊዎቹን ጠርቶ ትዕዛዝ መስጠት ሲገባው ዝም ብሎ ይዞ ከርሞ ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ውሳኔ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ክርክራቸው በአስተዳደሩ የተሰጠው ይዞታ ላይ ጥቅም ወይም መብት አለኝ፤›› የሚል በመሆኑ በሚመለከታቸው የአስተዳደሩ አካላት በይግባኝ ተዋረድ በተቀመጠው አግባብ ከሚጠይቁ በቀር፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሊታይ የሚችል አይደለም፤›› በማለት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ፋይሉን መዝጋቱን አሳውቀዋል፡፡ በመሆኑም የደረሰባቸውን የመልካም አስተዳደር በደል መንግሥት ተመልክቶ ፍትሕ እንዲሰጣቸው ባለይዞታዎቹ ጠይቀዋል፡፡ በደል እየደረሰባቸው የሚገኙት ባለይዞታዎች ያቀረቡትን አቤቱታ በሚመለከት ምላሽ እንዲሰጡበት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት፣ ከተማ ማደስ፣ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤቶችና የከተማ አስተዳደሩን ኃላፊዎች ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡  

 

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሥር ይተዳደራል የተባለው ኮርፖሬሽን ወደ ንግድ ሚኒስቴር ሊዛወር ነው

$
0
0

-ኮርፖሬሽኑ አምስት ኢንተርፕራይዞችን ይይዛል

በአዲሱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሥር ሆነው እንደሚቋቋሙና እንዲተዳደሩ ይደረጋሉ ከተባሉ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ፣ አምስት ኢንተርፕራይዞችን ይይዛል የተባለው የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ወደ ንግድ ሚኒስቴር ሊዛወር መሆኑ ተጠቆመ፡፡ 

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ተጠሪነታቸው ወደ ንግድ ሚኒስቴር እንዲዛወር ይደረጋል ተብለው የሚጠበቁት የኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት (አለ በጅምላ)፣ የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ አክሲዮን ማኅበር፣ የቀድሞ ጅንአድ (አሁን የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት) እና የኢትዮጵያ ግዥ አገልግሎት ድርጅቶች ናቸው፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ እነዚህ አምስት የመንግሥት ኢንተርፕራይዞች በኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጥላ ሥር ሆነው ከተዋቀሩ በኋላ፣ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሥር እንደሚሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡ 

ቀደም ብሎ በመንግሥት የተያዘው አወቃቀር ቀርቶ የአምስቱን ተቋማት ተጠሪነት ለመቀየር የታሰበው፣ ተቋማቱ የንግድ ሥራዎችን የሚያከናውኑ በመሆናቸው ወደ ንግድ ሚኒስቴር መዛወራቸው አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ነው ተብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት አምስቱን ተቋማት ያስተዳድራል የተባለው የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በመቋቋም ላይ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

የኮርፖሬሽኑ ተጠሪነት ወደ ንግድ ሚኒስቴር እንዲዛወር የሚያስችለው አዲሱ ጥናት ተጠናቅቆ ለሚኒስቴሮች ምክር ቤት ይቀርባል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ በቀረበው ጥናት መሠረት በሚኒስትሮች ምክር ቤትን ይሁንታ ካገኘ በኋላ ለፓርላማ ቀርቦ እንዲፀድቅ ይደረጋል ተብሏል፡፡ አዲሱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሲዋቀር በሥሩ ይተዳደራሉ ተብለው የተዘረዘሩት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር፣ የኢትዮጵያ ስኳርና የኬሚካል ኮርፖሬሽን ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪ የኮንስትራክሽን ሥራዎች፣ የግብርና ሥራዎች፣ የንግድ ሥራዎች፣ የኢትዮጵያ የነዳጅና ጋዝ ምርት አቅርቦትና የዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች ኮርፖሬሽን እንዲቋቋሙ ተደርጐ በሚኒስቴሩ ሥር ይተዳደራሉ ተብሎ ነበር፡፡

አሁን ግን በኮርፖሬሽን ደረጃ በመቋቋም ሥራቸውን ከጀመሩት ውስጥ የንግድ ሥራዎችን የሚመለከተው የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ወደ ንግድ ሚኒስቴር እንዲመጣ የሚደረግ በመሆኑ፣ በአዲሱ ሚኒስቴር ሥር የሚተዳደሩት አራቱ ኮርፖሬሽኖች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡  

 

በማታለል ወንጀል የተጠረጠሩት መምህር ግርማ ዋስትና ቢፈቀድላቸውም አልተፈቱም

$
0
0
በማታለል ወንጀል የተጠረጠሩት መምህር ግርማ ዋስትና ቢፈቀድላቸውም አልተፈቱም

በየካ ክፍለ ከተማ ኮተቤ በተለምዶ ወሰን ግሮሰሪ በመባል በሚታወቀው አካባቢ፣ የሚኖሩ ግለሰብን መኖሪያ ቤት በማሸጥና ገንዘባቸውንም ‹‹ፀሎት ይደረግበት›› በማለት አታለው ወስደዋል ተብለው ተጠርጥረው የታሰሩት [መምህር] ግርማ

ወንድሙ፣ ጥቅምት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በ50 ሺሕ ብር እንዲፈቱ የተፈቀደላቸው ቢሆንም፣ በተጠረጠሩበት ሌላ ወንጀል አልተፈቱም፡፡ 

ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር አድርጐ በመመርመር ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ቡድን፣ ጥቅምት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ባቀረበው የምርመራ ሥራው፣ ተጠርጣሪው ፈቃድ ማግኘት ከሚገባቸው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን (ቤተ ክህነት) ፈቃድ ሳያገኙ፣ በሐሰተኛ ሰነድ (ፎርጅድ) ሲገለገሉ እንደነበር አስረድቷል፡፡ 

በመሆኑም ቀሪ ምርመራ እንደሚቀረው ገልጾ፣ ከጠየቀው 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ሰባት ቀናትን ፈቅዶለታል፡፡ በመሆኑም [መምህር] ግርማ፣ ከቤት ሽያጭና ከሲም ካርድ ጋር በተያያዘ በቀረበባቸው ወንጀል በ50 ሺሕ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ በሐሰተኛ ሰነድ የተጠየቀባቸው የሰባት ቀናት ጊዜ የሚያልቀው ኅዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በመሆኑ በማረፊያ ቤት ለመቆየት ተገደዋል፡፡ 

 

የጥቅምት ወር የዋጋ ግሽበት በ11.8 በመቶ አሻቀበ

$
0
0

የጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በ11.8 በመቶ ማሻቀቡን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን የዋጋ መጨመር አዝማሚያ መታየቱን ኤጀንሲው ጠቁሟል፡፡

የአሁኑ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር የሚገኘው ውጤት፣ ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት ሁኔታን የሚያሳይ መሆኑን ኤጀንሲው ያስረዳል፡፡

የፍጆታ ዕቃዎችን ዋጋ ለማጥናት በአጠቃላይ 119 የገበያ ቦታዎች በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች መዳሰሳቸውን፣ የኤጀንሲው የጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. የዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ያስረዳል፡፡

በዚህም መሠረት የጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. የአገር አቀፍ ጠቅላላ የችርቻሮ ዋጋ ኢንዴክስ፣ ከጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ኢንዴክስ ጋር ሲነፃፀር በ11.8 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ለዚህ ጭማሪ ምክንያት የሆኑት ምግብና አልኮል ያልሆኑ መጠጦች በ16.2 በመቶ ዕድገት በማስመዝገባቸውና መጠጥ፣ ሲጋራና ትምባሆ በ11.3 በመቶ፣ ልብስና መጫሚያ በ7.1 በመቶ፣ የቤት ኪራይ፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ ውኃና ኢነርጂ ደግሞ 6.3 በመቶ በማስመዝገባቸው ነው፡፡

የቤት ዕቃዎች፣ የቤት ማስጌጫዎች፣ የቤት ቁሳቁሶችና የቤት ሠራተኛ ደመወዝ በ5.7 በመቶ፣ ሕክምና 7.8 በመቶ፣ መገናኛ 2.2 በመቶ፣ መዝናኛ 8.6 በመቶ፣ ትምህርት 14.7 በመቶ፣ ሬስቶራንትና ሆቴሎች 10.8 በመቶና ሌሎች ዕቃዎችና አገልግሎቶች በ5.3 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ በሌላ በኩል የትራንስፖርት የዋጋ ኢንዴክስ የ2.1 በመቶ ቅናሽ በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. መታየቱን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡  በተለይ ለዋጋ ግሽበት ከፍተኛ ተፅዕኖ የሆነው የምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት በአብዛኞቹ የምግብ ክፍሎች ላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ዳቦና እህል በ3.2 በመቶ፣ ሥጋ 14.1 በመቶ፣ ወተት፣ ዓይብና እንቁላል በ16.5 በመቶ፣ ዘይትና ቅባቶች በ16.6 በመቶ፣ ፍራፍሬ በ22.6 በመቶ፣ አትክልት፣ ጥራጥሬ፣ ድንችና ሌሎች ሥራ ሥሮች በ21.8 በመቶ፣ ስኳር፣ ማርና ቸኮሌት በ3.7 በመቶና ሌሎች ምግቦች በ74.5 በመቶ ዕድገት አሳይተዋል፡፡

ከፍተኛ የምግብ ዋጋ ጭማሪ የታየባቸው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል ገበያዎች ናቸው፡፡ አጠቃላይ አገራዊ የምግብ ዋጋ በ16.2 በመቶ ለማሻቀቡ ምክንያት  አዲስ አበባ በ30.3 በመቶ፣ ኦሮሚያ 23.7 በመቶ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ 22.0 በመቶ፣ አፋር 21.5 በመቶ፣ አማራ 11.1 በመቶ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡  

ላለፉት በርካታ ዓመታት መጠነኛ የዋጋ ግሽበት በመኸር ወቅት የተለመደ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ግን በርካቶች የአገሪቱ ሰብል አምራች አካባቢዎች በድርቅ የተመቱ በመሆናቸው፣ አጠቃላይ የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ከዚህ በላይ እንደሚያሻቅብ ባለሙያዎች ይገምታሉ፡፡             

 

ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ያቋቋመችው የቴክኒክ ኮሚቴ ከአሥር ቀናት በኋላ ለመገናኘት ወሰነ

$
0
0

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተፅዕኖዎችን ገለልተኛ ኩባንያ እንዲያጠና ለማድረግ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን የሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴ ዘጠነኛ ስብሰባውን ለሁለት ቀናት በግብፅ ካይሮ ቢያካሂድም፣ ስምምነት ላይ ባለመደረሱ ከአሥር ቀናት በኋላ ለመገናኘት ወሰነ፡፡

ስብሰባው ከጥቅምት 27 እስከ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ በግብፅ የተካሄደው፣ የተፅዕኖ ግምገማውን ለማድረግ ከተመረጡት ሁለት ኩባንያዎች መካከል ራሱን ከጥናቱ ያገለለው የኔዘርላንዱ ዴልታ ሬዝ ኩባንያ ምክንያቶችና አማራጭ መፍትሔዎች ላይ ተወያይቶ፣ ሦስቱንም አገሮች የሚያግባባ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ነበር፡፡ 

የኢትዮጵያን የቴክኒክ ኮሚቴ ቡድን የመሩት በቅርቡ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ሞቱማ መቃሳ ሲሆኑ፣ የዚህ ተቋም የቀድሞው ሚኒስትር በአሁኑ ወቅት የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው (በሚኒስቴር ማዕረግ) የተሾሙት አቶ ዓለማየሁ ተገኑም ተካተዋል፡፡

ውይይቱ ባለፈው ቅዳሜ ሲጀመር ንግግር ያደረጉት አቶ ሞቱማ፣ የህዳሴው ግድብ ተፅዕኖዎችን ለመገምገም የተመረጡት የፈረንሣዩ ቢአርኤል ኢንጂነርስና የኔዘርላንዱ ዴልታ ሬዝ ግምገማውን የሚያካሂዱበት መሪ ዕቅድ ቀርፀው ለመምጣት አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በመሆኑም በኢትዮጵያ በኩል ሦስት አማራጮች መኖራቸውን፣ አንደኛው አማራጭ የሁለቱን ኩባንያዎች ልዩነት በመፍታት አብረው እንዲሠሩ ማድረግ፣ ወይም ደግሞ የፈረንሣዩ ኩባንያ ብቻውን የተፅዕኖ ግምገማዎቹን እንዲያከናውን ማድረግ፣ አልያም ወደኋላ ተመልሶ በጨረታው ላይ ተሳትፈው ከነበሩ አማካሪ ድርጅቶች ሌሎች ሁለት ኩባንያዎችን መምረጥ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

በህዳሴው ግድብ ላይ የሚደረጉትን ሁለት የተፅዕኖ ግምገማ ጉዳዮች ማለትም ግድቡ በሱዳንና በግብፅ ላይ ሊኖረው የሚችለው የአካባቢያዊና የማኅበራዊ ተፅዕኖ፣ እንዲሁም የግድቡ ውኃ አያያዝና ኃይል አመነጫጨት (ውኃ አለቃቀቅ) በግብፅና ሱዳን ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመገምገም አራት ኩባንያዎች ማለትም ከፈረንሣይ ሁለት፣ ከኔዘርላንድና ከአውስትራሊያ አንድ አንድ ኩባንያዎች ተወዳድረው ነበር፡፡

የግብፅ የውኃና የመስኖ ሚኒስትር ሆሳም አል ሞግሃዚ በበኩላቸው፣ አንድ ኩባንያ ጥናቶቹን ያካሂድ በሚለው ላይ ግብፅ እንደማትስስማና በሚያዚያ ወር 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሦስቱ አገሮች ቴክኒክ ኮሚቴ የደረሰበትን ስምምነት የሚጥስ ነው ብለዋል፡፡  

በዚህ በሚያዚያ ስብሰባ ከተመረጡት ሁለት ድርጅቶች መካከል የፈረንሣዩ ቢአርኤል ኢንጂነርስ የሁለቱን ጥናቶች 70 በመቶ እንዲያከናውን፣ የፕሮጀክቱ ሕጋዊ ውል ተቀባይ ይኼው ኩባንያ በመሆኑ ብቻውን ጥናቱን ቢያካሂድ ችግር እንደሌለው ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡

ሌላኛው አማራጭ ወደኋላ ተመልሶ ሌሎች ኩባንያዎችን የመምረጥ ፍላጎት ጥናቱን የሚያጓትት ከመሆኑም በላይ፣ ኢትዮጵያ ግንባታውን በፍጥነት እያካሄደች በመሆኑ የጥናቱን ውጤት ለማካተት የሚያስችል አይሆንም በሚል ተቃውመውታል፡፡ 

በመሆኑም የቀረው አማራጭ የሁለቱን ኩባንያዎች ልዩነት መፍታት በመሆኑ፣ ከአሥር ቀናት በኋላ በሱዳን ካርቱም ለመገናኘት ተስማምተዋል፡፡

የኔዘርላንዱ ኩባንያ ዴልታ ሬዝ ራሱን ከጥናቱ ያገለለው በዋናው አማካሪ ድርጅት ቢአርኤል የተዘጋጀው መሪ ዕቅድ ሙያዊ ነፃነቱን እንደሚገፋበት በመግለጹ ነው፡፡ በቀጣዩ የሱዳን ስብሰባ የቴክኒክ ኮሚቴው ስምምነት ላይ ካልደረሰ፣ ጉዳዩ ወደ ሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሊመልስ እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡  

 

 

ሁለተኛው የቀላል ባቡር መስመር አገልግሎት ጀመረ

$
0
0
ሁለተኛው የቀላል ባቡር መስመር አገልግሎት ጀመረ

ከአያት አደባባይ - መገናኛ - ስታዲየም - ጦር ኃይሎች ድረስ የተዘረጋው የቀላል ባቡር መስመር፣ ማክሰኞ ጥቅምት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ንጋት ላይ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

ይኼ ከተማዋን ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚያካልለው ቀላል የባቡር መስመር፣ በቀን ለ16 ሰዓታት አገልግሎት እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡ በዚህ መስመር 21 ያህል ባቡሮች እንደሚሰማሩ የታወቀ ሲሆን፣ ታሪፉም ዝቅተኛው ሁለት ብር፣  መካከለኛው አራት ብር፣ ከፍተኛው ስድስት ብር ነው፡፡ ከመስከረም 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ከሰሜን ወደ ደቡብ ከተማዋን የሚያቆራርጠው የዳግማዊ ምንሊክ አደባባይ - ቃሊቲ መስመር የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡ የቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ 475 ሚሊዮን ዶላር ነው የተገነባው፡፡  መንግሥት ለቀላል ባቡር ግንባታ የወጣውን በብድር የተገኘ ገንዘብ ከሌሎች አማራጮች ማለትም ከአዲስ አበባ ውጪ ካሉ የባቡር መስመሮች ለመክፈል በማሰብ፣ በዓመት 1.5 ቢሊዮን ብር እንደሚደጉም መግለጹ አይዘነጋም፡፡ ይህም የተደረገው ነዋሪዎች አገልግሎቱን በርካሽ ታሪፍ እንዲያገኙ ለማድረግ መሆኑን፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በአጠቃላይ በሁለቱም አቅጣጫ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የቀላል ባቡር መስመር 32 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡

ፎተግራፍ፡- ዳንኤል ጌታቸውና ታምራት ጌታቸው 

 

ሁለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊዎች በሙስና ተጠርጥረው ተከሰሱ

$
0
0

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሐዋሳ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅና የደንበኞች አገልግሎት መኮንን፣ በሥልጣን ያላግባብ የመገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመሠረተባቸው፡፡ 

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው ሶስና ሀዲስ ገበየሁ (የደንበኞች አገልግሎት መኮንን)፣ አቶ ጌታቸው ዋቅሹም (የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በደቡብ ክልል መንግሥት ኦዲት ቢሮ የመዝገብ ቤት ሠራተኛ አቶ ፀጋዬ ግርማ ሲሆኑ፣ ክሱ የቀረበው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በጥቅም ተመሳጥረውና ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገል፣ የባንኩ ባልደረባ የሆኑት ወ/ሮ አለፊያ ከድር ለቤት መግዢያ ባንኩ የፈቀደላቸውን 320,000 ብር ለግል ጥቅም ማዋላቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ 

ተከሳሾቹ ባንኩ ለግለሰቧ የፈቀደውን ገንዘብ ቤቱን የሸጡላቸው ወ/ሮ ፅጌረዳ ሰይፉ አካውንት ማስገባት ሲገባቸው፣ በሁለተኛ ተከሳሽ ፀጋዬ ግርማ አካውንት ውስጥ በማስገባትና በተለያዩ ጊዜያት እያወጡ መጠቀማቸውም በክሱ ተገልጿል፡፡

የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ዋቅሹም፣ ገንዘቡ ለወ/ሮ ፅጌረዳ ሰይፉ ገቢ መደረጉን ሳያረጋግጡ በማፅደቃቸው፣ ከባድ ጉዳት በማድረስና ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት ወንጀል ተከሰዋል፡፡ አቶ ጌታቸው የተጠረጠሩበት ወንጀል ዋስትና እንደማያስከለክል ተገልጾ፣ በ3,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ በማዘዝ ለኅዳር 21 ቀን 2008 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

 

የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣን የነበሩት ተጠርጣሪ ለፓርላማና ለመንግሥት ደብዳቤ ጻፉ

$
0
0

-ከተጠርጣሪው ጋር የተከሰሱት አራት ተጠርጣሪዎች መጥፋታቸው ተገለጸ

የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባልና የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ወንድሙ ቢራቱ፣ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው እንዲያደርጉ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ለዕንባ ጠባቂ ተቋም ደብዳቤ ጻፉ፡፡

‹‹የሕገ መንግሥቱ የበላይነትና የኦሮሚያ ክልል የክስና የዳኝነት ሥልጣን ተጥሶ፣ የቀረበብኝን የሙስና ክስ ማንሳትና ፍትሕ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ ሰብዓዊ መብቴን ማስከበር›› በሚል ርዕስ በጻፉት ደብዳቤ እንደገለጹት፣ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የኦሕዴድ ኢሕአዴግ አባል በመሆን በመታገል ላይ ነበሩ፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ምክር ቤት አባልና የክልሉ ካቢኔ አባል በመሆን ለአሥር ዓመታት ማገልገላቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በክልሉ ሠራተኛና ባለሥልጣን ሆነው ሲሠሩ የፈጸሙት የሙስና ወንጀል ካለ ጉዳዩን የመመርመርና የመክሰስ ሥልጣን ያለው የክልሉ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሆኖ ሳለ፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መሆኑ ከሥልጣኑና ከሕግ ውጪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እሳቸው በተከሰሱበት ጉዳይ የዳኝነት ሥልጣን ያለው የክልሉ መንግሥት ፍርድ ቤት ቢሆንም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መከሰሳቸውን፣ ይኼም በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና አዋጅ ቁጥር 433/97 አንቀጽ (7) እና በአዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ (7) ሥር በግልጽ መደንገጉንም አቶ ወንደሙ በደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡ ግለሰብ ምንጊዜም ሊታመን ባይችልም ሕገ መንግሥቱና ተቋማት መከበር እንዳለባቸውና ይኼም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50(8) ተደንግጐ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ ጥፋት ካለባቸው እንደሚከሰሱ እንደሚያውቁ የገለጹት አቶ ወንድሙ፣ እየጠየቁ ያለው ሥልጣን ባለው አካል ተከሰው ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት የመዳኘትና ፍትሕ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው መሆኑን በደብዳቤያቸው አስረድተዋል፡፡

አቶ ወንድሙ በክልሉ የፀጥታ ቢሮ የሚሊሺያና የተጠባባቂ ጦር ዘርፍ ኃላፊ ሆነው ከመሥራታቸውም በተጨማሪ፣ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሠራተኛ፣ ምክትል ኃላፊና የቢሮ ኃላፊ፣ እንዲሁም የብድርና ቁጠባ ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው መሥራታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ሆነው በሚሠሩበት ወቅት የክልሉ ገቢ ሰብሳቢ ጽሕፈት ቤቶችን በኔትወርክ በማያያዝና ተገቢውን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በመዘርጋት፣ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ከፍተኛ ገቢ በማስገኘታቸው ምሥጉን ሠራተኛ ሆነው ተሸላሚ እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከነሐሴ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ አስሮና ከሷቸው የሚገኘው፣ በአሳሳችና ጐጂ የቂም በቀለኞች ሐሰተኛ ጥቆማ መነሻነት መሆኑንም አቶ ወንድሙ የግለሰቦቹን ስም በመጥቀስ ገልጸዋል፡፡ 

ተከሳሽ አቶ ወንድሙ ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥቆማ በመስጠት እንዲታሰሩ ያደረጉ ሁለት ግለሰቦችንና ለምን ኮሚሽኑን እንዳሳሳቱት በዝርዝር የጠቀሱ ሲሆን፣ ለመንግሥት 19 ዓመታት ሠርተው ያገኙት ገቢ 889,976 ብር ብቻ ተብሎ መጠቀሱን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ የመጀመሪያ የሠራተኝነት ደመወዛቸውን በ19 ዓመታት ከማባዛት ውጪ በሹመት ያገኙት ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ያልተጨመረበት መሆኑን አክለዋል፡፡

የቀረበባቸው ክስ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(1)(2) እንዲሁም በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ/122 መሠረት ክሱ እንዲነሳላቸውና ትኩረት እንዲሰጡላቸው ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎች፣ ለክልሉ መንግሥት ፕሬዚዳንትና አፈ ጉባዔ፣ ለኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ደብዳቤያቸው እንዲደርስ አድርገዋል፡፡ በግልባጭ የክልሉ መንግሥት ምክር ቤት፣ የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ ኦሕዴድ፣ ኢሕአዴግና የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲያውቁት አድርገዋል፡፡

በሌላ በኩል የአቶ ወንድሙን ክስ እያየው የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ከአቶ ወንድሙ ጋር ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸውን ነገር ግን እጃቸው ያልተያዙት አቶ ባህሩ ቢረዳ፣ ሸዋረገድ ቢረዳ፣ እልፍነሽ ቢራቱና ባለቤታቸው ወ/ሮ አሰገደች መንግሥቱን አፈላልጐ ለጥቅምት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የታዘዘው ኮሚሽኑ እንዳላገኛቸው ገልጿል፡፡ በምርመራም ወቅት አለመገኘታቸውና እስካሁን በክትትል ላይ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ በተገኙ ጊዜ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ፍርድ ቤቱን በደብዳቤ ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም አቶ ወንድሙ የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ፣ አስፈላጊ ሰነዶች በሚታይ ሁኔታ ኮፒ ተደርጐ እንዲሰጣቸው፣ የኮሚሽኑ ምርመራና ክትትል ቡድን ያልተያዙትን ተከታትሎ በመያዝ አስሮ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት፣ የአቶ ወንድሙን የክስ መቃወሚያ ለመስማትና ያልተያዙትን ለመጠባበቅ ለኅዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡      

 
Viewing all 1779 articles
Browse latest View live