Quantcast
Channel: ዜና
Viewing all 1779 articles
Browse latest View live

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ድርጅትን ወቀሰ

$
0
0

-የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለማስተላለፍ እንቅፋት ሆኗል አለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ችግሮችን ለመቅረፍ የጀመራቸው ፕሮጀክቶች በአግባቡ እንዳይከናወኑ፣ ዋነኛ እንቅፋት ሆኗል የተባለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ ወቀሳ ቀረበበት፡፡

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማኔጅመንትን ሲያስተዳድር የቆየው የህንዱ ፓወር ግሪድ ኮርፖሬሽን፣ ችግሩን ለመቅረፍ ተጨባጭ እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻሉን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ ተናግረዋል፡፡ 

አቶ መኩሪያ ይህንን የተናገሩት ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡

ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለሁለት ከመከፈሉ በፊት ሲንከባለል የመጣ ችግር ነበር፡፡ በተለይም ኮርፖሬሽኑ ለሁለት ተከፍሎ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን የህንዱ ኩባንያ ከያዘው በኋላም ችግሩ ከመፈታት ይልቅ የበለጠ ተወሳስቧል፡፡ 

በአዲስ አበባ አስተዳደርና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መካከል የተፈጠረው ችግር ምክንያት ለኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታም ሆነ፣ ግንባታው ከተከናወነ በኋላ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ያለመኖሩ ነው፡፡ 

በቅርብ ጊዜ እንኳ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 35 ሺሕ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ዕጣ ቢያወጣም፣ መኖሪያ ቤቶቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊገባላቸው ባለመቻሉ ለተጠቃሚዎቹ ማስተላለፍ አልተቻለም፡፡ በቅርቡ ለነዋሪዎች ይተላለፉ የተባሉት 40 ሺሕ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ከ90 በመቶ በላይ ግንባታቸው ቢጠናቀቅም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊቀርብ ባለመቻሉ ብቻ ዕጣ ማውጣት አልተቻለም ብለዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኃይለ ማርያም በግምገማው ወቅት እንደተናገሩት፣ 35 ሺሕ ቤቶችን ዕጣ በማውጣትና ባለማውጣት ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለበት በተካሄደ ውይይት ላይ፣ ድርጅቱ ዕጣው እንዲወጣ መተማመኛ ሰጥቷል፡፡ “ነገር ግን እስካሁን ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመቅረቡ ቤቱቹን ለዕድለኞች ማስተላለፍ አልቻልንም፤” ሲሉ አቶ ጌታቸው ድርጅቱን ወቅሰዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ከ90 በመቶ በላይ የተጠናቀቁትን 40 ሺሕ ቤቶች ዕጣ ለማውጣት ተቸግረናል፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ እየቀረበ ያለው ወቀሳ ሁለት መነሻ ምክንያቶች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ በሚካሄድበት ወቅት የኤሌክትሪክ ምሰሶና ትራንስፎርመር አለማቅረብ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የቤቶች ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞችና ዋነኛ የግንባታ ተዋናዮች በተለያዩ ችግሮች ውስጥ አልፈው ለገነቧቸው ቤቶች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችሉ ግንባታዎችን በወቅቱ አለማካሄድና እንዲሁም ኃይል አለማቅረብ የሚሉት ችግሮች ናቸው፡፡ 

የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ድርጅት ለኃይል ግንባታ የሚሆኑ መሣሪያዎችና የኤሌክትሪክ ኃይል በበቂ ሁኔታ እንዳለውና እንደሌለውም በውል እንደማይታወቅ ባደረጓቸው የሥራ ግንኙነቶች መረዳት እንዳልቻሉ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ባለሥልጣናት በግምገማው ወቅት አስረድተዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ የመሬት ዝግጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሃይማኖት ወልደ ገብርኤል እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጀት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አለበት ለማለት ያስቸግራል፡፡ ወ/ሮ ሃይማኖት ምክንያታቸውን ሲያድረዱ፣ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ድርጅት በከተማው ውስጥ ሕገወጥ ግንባታ ላካሄዱ ግለሰቦች የኤሌክትሪክ ኃይል ያስገባል ብለዋል፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በሕገወጥ መንገድ የተገነቡ የጨረቃ ቤቶች በ2003 ዓ.ም. እንዲፈርሱ በተደረገበት ወቅት፣ የኤሌክትሪክ ኃይልም ተቋርጦባቸው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ሕገወጦቹ ጨረቃ ቤቶቹን መልሰው የገነቡ በመሆናቸው፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ገብቶላቸዋል በማለት ወ/ሮ ሃይማኖት ተናግረዋል፡፡ 

“በሕጋዊ መንገድ ግንባታ ላካሄዱ ግለሰቦችና ለኮንዶሚኒየም ቤቶች የኤሌክትሪክ ኃይል ማስገባት አለመቻል ድርጅቱ የማኔጅመንት ችግር እንዳለበት የሚያሳይ ነው፤” ሲሉ ወ/ሮ ሃይማኖት ተችተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የህንዱ ኩባንያ የማኔጅመንት ጊዜውን አጠናቆ የተሰናበተ ሲሆን፣ በምትኩ በአቶ ጎሳዬ መንግሥቴ የሚመራ አዲስ ማኔጅመንት ተሰይሟል፡፡ 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጎሳዬ መንግሥቴ ችግሩን አምነዋል፡፡ አቶ ጎሳዬ እንዳስረዱት፣ የአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኔትወርክ እንደገና መታየት አለበት፡፡ ከኔትወርኩ በተጨማሪም የአዳዲስ የማስተላለፊያና የማሰራጫ ጣቢያዎች ግንባታ መካሄድ አለበት፡፡ “የተነሱት ነጥቦችን ወስደን እናስተካክላለን” በማለት የተናገሩት አቶ ጎሳዬ፣ ‹‹የማኔጅመንት ችግሩን በመፍታት ከአስተዳደሩ ጋር እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡   

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሥረኛውን ዙር የቤቶች ዕጣ ያወጣው በሚያዝያ 2007 ዓ.ም. ነው፡፡ ዕድለኞቹ ቤታቸውን መረከብ ሳይችሉ ሰባት ወራት የተቆጠሩ ሲሆን፣ ይህም ለተለያዩ ችግሮች እንደዳረጋቸው እየተናገሩ ነው፡፡ 

 

አክሰስ ሪል ስቴት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ባለመጀመሩ ደንበኞች ሥጋት ውስጥ ገብተዋል

$
0
0

የአክስስ ሪል ስቴት ኩባንያ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ወደ አገር ከተመለሱ በኋላ አንዳች መፍትሔ ያመጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ ኩባንያው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ባለመጀመሩ ሥጋት እንደፈጠረባቸው ቤት ገዢዎች ገለጹ፡፡

አቶ ኤርሚያስ መንግሥት የሕግ ከለላ ሰጥቶአቸው ከተመለሱ ስምንት ወራት ቢቆጠሩም፣ ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ ባለመታየቱ ተስፋቸው በድጋሚ እየጨለመ መምጣቱን የአክሰስ ሪል ስቴት ቤት ገዢዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ምንጮች እንደገለጹት፣ አቶ ኤርሚያስ የአክሰስ ሪል ስቴት ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ለተቋቋመው በከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ለሚመራው ዓብይ ኮሚቴ ዕቅዳቸውን አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን የዓብይ ኮሚቴው አባላት በተለያዩ የፓርቲና መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ተጠምደው፣ ላለፉት አራት ወራት መሰብሰብ ባለመቻላቸው በዕቅዱ ላይ እስካሁን ውይይትም ሆነ ውሳኔ አልተላለፈም፡፡ 

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደጠቆሙት፣ ዓብይ ኮሚቴው ተሰብስቦ ውሳኔ ባለማሳለፉ አሁን በቦታው ላይ የሚገኙ አንዳንድ የቦርድ አባላትና የቤት ገዥዎች ተወካይ ነን የሚሉ ግለሰቦች በአክሰስ ሪል ስቴት ውስጥ ውዝግብ በማስነሳት ችግር እየተፈጠረ መሆኑ እንዳሳሰባቸው የቤት ደንበኞች ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ምንጮች እንደገለጹት፣ ዓብይ ኮሚቴው ውሳኔ ያልሰጠበት የዕቅድ ሰነድ እንደሚተነትነው አቶ ኤርሚያስ ከሦስት ኩባንያዎች ጋር ሲያካሂዱ የቆዩትን ድርድር አገባደዋል፡፡

የመጀመሪያው በአያት፣ በሲኤምሲ፣ በኒያላ ሞተርስ፣ በለቡና በመገናኛ አካባቢ ሰንራይዝ ሳይቶች የግንባታ ሥራዎችን በፍጥነት መጀመር ነው፡፡ በተለይ በመገናኛ ሰንራይዝ ያለው ግንባታ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ሊጀመር እንደሚችልና የሚገነባውም ግንባታ ወደ 19 ፎቅ ለማሳደግ መታቀዱ ተገልጿል፡፡ ይኼንን ለማከናወን የሕንፃዎች ዲዛይን የተሠራ ሲሆን፣ ይህን ግንባታ ለማካሄደ ከቻይናው ሂቢል ፒንግ ሪል ስቴት ኩባንያ ጋር ሽርክና ለመፈጸም የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን የአቶ ኤርሚያስ ዕቅድ ሰነድ እንደሚያስረዳ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ የቻይናው ሂቢል ፒንግ 60 ሚሊዮን ዶላር ለማቅረብ መወሰኑንና ገንዘብም ለቅረብ እንደሚቻልም ማስረጃ ማቅረቡን ምንጮች ጠቁመው፣ ይኼ ግንባታ ከተካሄደ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ቤት ገዢዎች እንደሚውል ማሳወቁን አስረድተዋል፡፡ 320 ቤቶች ያሉት የኒያላ ሞተርስ ሳይት ከአራት ወራት ግንባታው መጀመር የነበረበት ቢሆንም በችግር ፈጣሪዎች ምክንያት እስካሁን አልተጀመረም ተብሏል፡፡

ሌላኛው የአቶ ኤርሚያስ ዋነኛ አጋር እንደሆነ የተነገረለት የቻይናው ሲሲኢሲሲ ኩባንያ ነው፡፡ ይኼ ኩባንያ በሁለም ሳይቶች የቤቶች ግንባታ ለማካሄድ ማቀዱ የተገለጸ ሲሆን፣ ኩባንያው ኢትዮጵያ ውስጥ በባቡር መስመርና በኢንዱስትሪ ዞኖች ግንባታ የተሰማራ የቻይና ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡

ይኼ ኩባንያ የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበርን ከፍተኛ አክሲዮን ለመግዛትና የሁሉንም የአክሰስ ሪል ስቴት ፕሮጀክቶች ለመገንባት ፍላጎት ማሳየቱን ለዓብይ ኮሚቴው በቅርቡ የቀረበ የዕቅድ ሰነድ ላይ መገለጹን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሲሲኢሲሲ የአክሰስ ሪል ስቴት ማኔጅመንት የሚረከብ መሆኑንም ሰነዱ ማብራራቱን ምንጮች ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ለአክሰስ ሪል ስቴት ግንባታዎች አስፈላጊ የሆኑ የገንዘብ አቅርቦትና የግንባታ አቅም የተገኘ መሆኑን፣ የአፈር ፍተሻና የሕንፃ ዳግም ዲዛይን ሥራ እንዲሠራ ኢቲጂ ተመርጧል፡፡ ኢቲጂ ይኼንን ሥራ በብድር ለመሥራት የተሰማማ መሆኑ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

አክስስ በአብዛኛው የነበሩበት የቦታ ጉዳዮችና የፍርድ ቤት ክርክር በጥሩ ሁኔታ በመወጣት ላይ መሆኑን ለዓብይ ኮሚቴው የቀረበው ሰነድ እንደሚያመለክት፣ ነገር ግን አቶ ኤርሚያስ እነዚህን ችግሮት ለመፍታት ጥረት ቢያደርጉም፣ በተለይ በቦርድ ውስጥ ባሉ የተወሰኑ አባላት ችግር እየገጠማቸው መሆኑን፣ የቤት ደንበኞች የሆኑት እነዚህ ምንጮች መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡

የሥራ አመራር ቦርዱ አቶ ኤርሚያስን ከቦርድ ሰብሰቢነት እንዳነሳቸውና የሥራ አመራር ቦርዱ ይኼንን ውሳኔ ያሳለፈው አምስት ለሁለት በሆነ ድምፅ መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም አቶ ኤርሚያስ የተነሱበት ቃለ ጉባዔ፣ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት አልተረጋገጠም ተብሏል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ቃለ ጉባዔውን እስካልተረጋገጠ ድረስ የቦርዱ ሊቀመንበር አቶ ኤርሚያስ መሆናቸው  ለዓብይ ኮሚቴው ተተንትኗል፡፡

 ነገር ግን አቶ ኤርሚያስ ከቦርድ እንደተነሱ ተደርጎ መነገሩ ከቻይና ኩባንያዎች ጋር የሚያደርጉት ድርድር ላይ እንከን የሚፈጥር በመሆኑ፣ ዓብይ ኮሚቴው ፈጣን ዕርምጃ በመውሰድ የቤት ደንበኞችን ፍላጎት እንዲያሟላ ጥያቄ እየቀረበ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ቤት ገዢዎች በአሁኑ ወቅት የአክሰስ ሪል ስቴት ቦርድ ምን እየሠራ ነው? የቴክኒክ ኮሚቴውስ? የዓቢይ ኮሚቴው አባላት ለረጅም ጊዜ በተለያዩ የአገር ጉዳዮች በመጠመዳቸው ምክንያት የአክሰስ ሪል ስቴት ጉዳይ ስለተዘነጋ፣ አሁን አዲሱ መንግሥት ከተመሠረተ ወዲህ ምን እየሠሩ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን እያነሱ ነው፡፡ አቶ ኤርሚያስ ከውጭ ከመጡ በኋላ ተረጋግቶ የነበረው አክሰስ ሪል ስቴት አሁን ሥጋት እያንዣበበት ስለሆነ፣ አቶ ኤርሚያስ በየደረጃው ያቀረቡት ዕቅድና የሥራ አፈጻጸም በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ፣ ዓብይ ኮሚቴው በመንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት እንዲወጣ የቤት ገዢዎች ጠይቀዋል፡፡ በአክሰስ ሪል ስቴት ውስጥ ሥራ እያደናቀፉ ያሉና የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያሳድዱ ሰዎችም በሕግ እንዲባሉ ዓቢይ ኮሚቴውን ተማፅነዋል፡፡

የዓብይ ኮሚቴ አባላት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር፣ የፍትሕ ሚኒስትር፣ የንግድ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ አማካሪ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ናቸው፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴውም ከእነዚህ መሥሪያ ቤቶች የተወጣጡ ተወካዮች ናቸው፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ የንግድ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ኑረዲን መሐመድ ናቸው፡፡ ዓብይ ኮሚቴው በቅርቡ ተሰብስቦ ውሳኔ እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአክሰስ ሪል ስቴት ወቅታዊ ሁኔታና በቦርድ አባላትና የገዢዎች ወኪል ነን በሚሉ ግለሰቦች እየተፈጸመ ስላለው ጉዳይ አቶ ኤርሚያስ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

 

ሳሊኒ የግንባታ ውል ሳይፈራረም በአዲሱ ጊቤ አራት የኃይል ፕሮጀክት ቁፋሮ መጀመሩ ተሰማ

$
0
0
ሳሊኒ የግንባታ ውል ሳይፈራረም በአዲሱ ጊቤ አራት የኃይል ፕሮጀክት ቁፋሮ መጀመሩ ተሰማ

በኢትዮጵያ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግንባታዎችን በማካሄድ የሚታወቀው ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የግንባታ ውል ሳይፈራረም በጊቤ አራት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሲቪል ምህንድስና ሥራ መጀመሩን ምንጮች ገለጹ፡፡ 

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ጊቤ አራትን በሚመለከት ሐምሌ 2007 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የመግባቢያ ሰነድ (MOU) ተፈራርሟል፡፡ ነገር ግን የመግባቢያ ሰነድ የአዋጭነትና የዲዛይን ጥናቶችን እንዲያካሂድ እንጂ ግንባታ የሚያስጀምረው አይደለም፡፡ 

ነገር ግን ከሥፍራው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን የአፈር ቆረጣ ሥራዎችን በማካሄድ የሲቪል ምህንድስና ሥራዎችን እያካሄደ ነው፡፡

የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ኮሜርሻል መምርያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ብርሃኔ ለሪፖርተር እንደገለጹት ግን፣ ድርጅታቸው እየሠራ የሚገኘው ወደ ሳይቱ የሚወስደውን መንገድ እንጂ የሲቪል ምህንድስና ሥራዎችን አይደለም፡፡ ምንጮች በአቶ ሰለሞን አስተያየት አይስማሙም፡፡ 

ከሳሊኒ በተጨማሪ በጊቤ አራት ፕሮጀክት ላይ ጥናት እንዲያካሂዱ አምስት የቻይና ኩባንያዎች በደብዳቤ ተጠይቀዋል፡፡ ምንጮች እንደገለጹት፣ እነዚህ ኩባንያዎች የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ አዝማሚያ ሥራው እንደተሰጠው የሚያስመስለው በመሆኑ፣ እነሱ የሚያከናውኑት ጥናት ባዶ ልፋት እንዳይሆንባቸው ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡ 

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ለግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከአውሮፓ የፋይናንስ ተቋማት ያገኛል የሚል እምነት መኖሩን የሚያመለክቱት ምንጮች፣ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ሬንዜ በሐምሌ 2007 ዓ.ም. ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት በጊቤ አራት ፕሮጀክት ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ተነጋግረዋል ይላሉ፡፡ 

በዚህ ውይይት ሳሊኒ ለዚህ ፕሮጀክት ፋይናንስ እንደሚያገኝ የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መተማመኛ መስጠታቸውን የሚናገሩት ምንጮች፣ በዚህ ምክንያት ሳሊኒ ወደ ግንባታ ለመግባት እንደተደፋፈረ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ 

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ጊቤ አንድ፣ ጊቤ ሁለት፣ ጊቤ ሦስትና ጣና በለስ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ግንባታ ፕሮጀክቶችን ያካሄደ ግዙፍ ተቋም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ምልክት በሆነው ዓባይ ወንዝ ላይ የሚካሄደውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር በመሆን እየገነባ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሳሊኒ የገነባው ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ሰሞኑን ለሙከራ 70 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የጀመረ ሲሆን፣ ሳሊኒ ቀጣይ ማረፊያውን ጊቤ አራት ላይ ማድረጉ ነው የሚነገረው፡፡ ምንጮች እንደሚሉት፣ ለጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ከውጭ አበዳሪዎች ይጠበቅ የነበረው ፋይናንስ በአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ውትወታ ምክንያት ባለመገኘቱ፣ ሳሊኒ በኢትዮጵያ መንግሥት በጀት የጊቤ ሦስትን ሲቪል ምህንድስና ለማከናወን ተገዷል፡፡ 

ጊቤ አራት በደቡብ ክልል በቱርካና ሐይቅ አቅራቢያ የሚገነባ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት እውን ከሆነ ኢትዮጵያ 1,450 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ታገኛለች ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ጊቤ አምስት የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግንባታ ከተካሄደ የማመንጨት አቅሙ 600 ሜጋ ዋት እንደሚሆን የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ጥናት ያመለክታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት ሊገኙ ባለመቻላቸው ምክንያት አልተሳካም፡፡ 

 

ብሔራዊ ባንክ የዓባይ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሹመት አፀደቀ

$
0
0

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለዓባይ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንትነት የታጩትን የአቶ በለጠ ዳኘውን ሹመት ማፅደቁ ተገለጸ፡፡ ከባንኩ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የአቶ በለጠ ሹመት የፀደቀው የዓባይ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ጥያቄው

ባቀረበ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ሹመቱ የፀደቀላቸው አዲሱ የዓባይ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ወደ ባንኩ ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ፣ የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የቅርንጫፍ ማስተባበሪያ መምርያ ዳይሬክተር በመሆን ለስድስት ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ 25 ዓመታት ማገልገላቸው የተገለጸው አቶ በለጠ፣ ኢንዱትሪውን የተቀላቀሉት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቀጠር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሥር ዓመት የሠሩ ሲሆን፣ በኃላፊነት ደረጃም የባንኩ የቅርንጫፍ መመርያ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ያገለግሉ እንደነበር የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

 በአቢሲኒያ ባንክ ውስጥም በተመሳሳይ የኃላፊነት መደብ የቅርንጫፎች መምርያ ኃላፊና የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሲያገለግሉ እንደነበር ታውቋል፡፡

አቶ በለጠ በኢኮኖሚክስ የመጀመርያ ዲግሪ፣ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው፡፡

በምክትል ፕሬዚዳንትነት የተሾሙበት ዓባይ ባንክ ከ3,300 በላይ ባለአክሲዮኖች ሲኖሩት፣ ከ90 በላይ ቅርንጫፎች አሉት፡፡

 

 

በአዲስ አበባ ለሰው ሕይወት አደጋ የሆኑ ጉድጓዶች እንዲከደኑ ትዕዛዝ ተሰጠ

$
0
0
በአዲስ አበባ ለሰው ሕይወት አደጋ የሆኑ ጉድጓዶች እንዲከደኑ ትዕዛዝ ተሰጠ

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ተቆፍረው ሳይከደኑ ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት እየሆኑ ያሉ ጉጓዶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲከደኑ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተካሄደ ስብሰባ ላይ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ለሁሉም የመሠረተ ልማት ተቋማት በቃል በሰጡት ትዕዛዝ፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እነዚህ ጉድጓዶች መከደን አለባቸው፣ ይህን ያላደረገ ተቋም ግን ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

በተለያዩ የኮንዶሚኒየም ሳይቶች ተከፍተው የሚገኙ ጉድጓዶች ለሕፃናት ሞት ምክንያት ሆነዋል፡፡ በቅርቡ በአያት ቁጥር ሁለት ኮንዶሚየምና በጀሞ ኮንዶሚኒየም ባልተከደኑ ጉድጓዶች የሕፃናት ሕይወት አልፏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ዙሪያ ልዩ ልዩ የግንባታ ማዕድናት ከወጡባቸው በኋላ ክፍት ሆነው የሚገኙት ትላልቅ ጉድጓዶች፣ ውኃ እያቆሩ በሚፈጥሩት ኩሬ  የሰው ሕይወት እያለፈ ነው፡፡ 

አቶ መኩሪያ ተከፍተው በተተው ጉድጓዶች ሕይወታቸው ባለፈ ሕፃናት ምክንያት እጅግ ማዘናቸውንና የልጃቸው ሕይወት ያለፈ ያህል እንደተሰማቸው ገልጸው፣ እነዚህ ጉድጓዶች ክፍታቸውን ሊቀመጡ እንደማይገባና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲከደኑ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ጉድጓድ በመቆፈር የሚታወቁት ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣንና የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ናቸው፡፡

በእነዚህ አራት የመሠረተ ልማት ተቋማት በኩል መናበብና በጋራ ዕቅድ ላይ የተመሠረተ ግንባታ ስለማይካሄድ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለቁጥር የሚያታክቱ ጉድጓዶች እንዲገኙ ምክንያት እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡

እነዚህ ጉድጓዶች ተከፍተው በመተዋቸው ለሕፃናት፣ ለአረጋውያንና ለአካል ጉዳተኞች የሥጋት ቀጣና ሆነዋል ተብሏል፡፡ የመሠረተ ልማት ተቋማቱን በፌዴራል ደረጃ የሚያስተባብር ተቋም እንዲመሠረት መወሰኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ይህ ተቋም ሲመሠረት የመሠረተ ልማት ተቋማቱ ቀጣይ ሥራቸውን እየተናበቡ እንደሚያካሂዱ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከዚያ በፊት የተቆፈሩና ያልተከደኑ ጉድጓዶችን እንዲከድኑ በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ጠንካራ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

 

በሳዑዲ ዓረቢያ የሐጅ ፀሎት ሕይወታቸውን ላጡ 53 ዜጐች የፀሎት ሥነ ሥርዓት ይደረጋል

$
0
0
በሳዑዲ ዓረቢያ የሐጅ ፀሎት ሕይወታቸውን ላጡ 53 ዜጐች የፀሎት ሥነ ሥርዓት ይደረጋል

መስከረም 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በሳዑዲ ዓረቢያ የሐጅ ፀሎት ወቅት ሚና በተባለው ቅዱስ ሥፍራ በደረሰው አደጋ የሞቱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 53 መድረሱን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

ለሟቾች በመጪው ዓርብ ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. አገሪቱ ውስጥ በሚገኙ መስጊዶች በሙሉ የፀሎት ሥነ ሥርዓት ይከናወናል ተብሏል፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ አሚን ጥቅምት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የእስልምና ዕምነት ተከታዮችና የሃይማኖት አባቶች በሚደረገው የፀሎት ሥነ ሥርዓት ሟቾችን እንዲያስቡ አሳስበዋል፡፡ 

በዘንድሮ የሐጅ ፀሎት ላይ ለመሳተፍ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ከሄዱ አሥር ሺሕ ኢትዮጵያውያን የዕምነቱ ተከታዮች መካከል፣ 53 ያህሉ በአደጋው ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተረጋግጧል፡፡ 

የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በሰጠው መግለጫ መሠረት፣ 48 ሟቾች ለሐጂ ፀሎት የሄዱበት ሥፍራ ቅዱስ በመሆኑ ሥርዓተ ቀብራቸው እዚያው እንዲፈጸም ቤተሰቦቻቸው በማሳሰባቸው ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ 

በሐጅ የፀሎት ሥነ ሥርዓት ወቅት በተፈጠረው መጨናነቅና መረጋገጥ ሕይወታቸው ካለፈው 53 ኢትዮጵያውያን መካከል 43ቱ ከኢትዮጵያ የተጓዙ ናቸው፡፡ አሥሩ ደግሞ በሳዑዲ ዓረቢያ ነዋሪ መሆናቸውን ከመግለጫው ለመረዳት ተችሏል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ከመላው ዓለም ለሐጅ ፀሎት ከተሰባሰቡት ሁለት ሚሊዮን ያህል የዕምነቱ ተከታዮች መካከል፣ እስካሁን 2,177 ያህሉ መሞታቸው መረጋገጡን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርና አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ናይፍ አደጋው የደረሰበትን ቦታ ባለፈው እሑድ ሲጎበኙ፣ የአደጋው መንስዔ በጥብቅ እየተመረመረ መሆኑን መግለጻቸው ተነግሯል፡፡

ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት በደረሱ አደጋዎች የዕምነቱ ተከታዮች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የዘንድሮው ግን እጅግ የከፋ ነው ተብሏል፡፡ በሚና ከደረሰው ቀደም ብሎ መካ ውስጥ በተከሰተ የክሬን ተገርስሶ መውደቅ አደጋ 111 ሰዎች ሞተዋል፡፡ 

በዘንድሮው አደጋ ኢራን 465፣ ማሊ 254፣ ናይጄሪያ 199፣ ግብፅ 182፣ ካሜሩን 76፣ ኒጀር 72፣ ሴኔጋል 61፣ ኢትዮጵያ 53፣ አይቮሪኮስትና ቤኒን 52፣ ሱዳን 30፣ ታንዛኒያ 20፣ ሶማሊያ 10 ዜጐች ከሞቱባቸው አገሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡   

 

ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለጉዳት ካሳ ከ2.4 ቢሊዮን ብር በላይ ከፈሉ

$
0
0

በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ በ2007 በጀት ዓመት ለጉዳት ካሳ ከ2.4 ቢሊዮን ብር በላይ መክፈላቸው ታወቀ፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የ2007 ዓ.ም. የመጀመርያ ደረጃ የኦዲት ሪፖርት  እንደሚያመለክተው፣ በበጀት ዓመቱ ከተከፈለው የጉዳት ካሳ ውስጥ ከ65 በመቶ በላይ የተከፈለው ለሞተር ወይም ከተሽከርካሪዎች አደጋ ጋር ለተያያዘ ጉዳት ነው፡፡

ኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ከተሽከርካሪዎች አደጋ ጋር በተያያዘ የሚከፍሉት የካሳ ክፍያ አሁንም ለውጥ ሳያሳይ መቀጠሉን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ 

ኩባንያዎቹ ከሰጡት የኢንሹራንስ ሽፋን ውስጥ 94 በመቶ ሕይወት ነክ ላልሆኑ ኢንሹራንስ ዘርፎች ሲሆን፣ ስድስት በመቶው ብቻ ለሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን የተሰጠ ነው፡፡

ኩባንያዎቹ በተጠቀሰው በጀት ዓመት ያሰባሰቡት የዓረቦን መጠን 5.5 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በጥቅል ካሰባሰቡት ዓረቦን ውስጥ ከ5.3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ሕይወት ነክ ካልሆነ የመድኅን ሽፋን የተሰበሰበ ነው፡፡ ከ315 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ ከሕይወት ኢንሹራንስ የመድን ሽፋን የተሰበሰበ ነው፡፡ 

ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በበጀት ዓመቱ ከ823 ሚሊዮን ብር በላይ ከታክስ በፊት ማትረፍ እንደቻሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ትርፉ ቀደም ካለው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ 

ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት 17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የመንግሥት ሲሆን፣ የቀሩት በባለአክሲዮኖች የተደራጁ የግል ኩባንያዎች ናቸው፡፡

 

 

 

 

 

 

የኦርቶዶክስ ገቢ በቢሊዮን ቢቆጠርም የምዕመናኑ ቁጥር እየቀነሰ መሆኑ ተገለጸ

$
0
0
የኦርቶዶክስ ገቢ በቢሊዮን ቢቆጠርም የምዕመናኑ ቁጥር እየቀነሰ መሆኑ ተገለጸ

-‹‹ምዕመናንን የመጠበቅ ተልዕኮ እየተወጣን አይደለም›› አቡነ ማትያስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሰበካ ጉባዔ መደራጀት ስትጀምር ገቢዋ በመቶ ሺሕ ብር የነበረ ቢሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ወደ ቢሊዮኖች ብር ማደጉን የገለጹት ፓትርያርኩ አቡነ ማቲያስ፣ የምዕመናኗ ቁጥር ግን እየቀነሰ መሆኑን አስታወቁ፡፡ 

ፓትርያርኩ 34ኛውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔን አስመልክቶ ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ጊዜ ያለው የቤተ ክርስቲያኗ ገቢ በቂ ነው ባይባልም፣ በየጊዜው እያደገ መጥቶ ከመቶ ሺዎች ብር ወደ ቢሊዮኖች ብር አድጓል፡፡ ይኼ የሆነውም ቤተ ክርስቲያኗ ከልጆቿ (ምዕመናን) ከምታገኘው ገቢ ባለፈ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፏ ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የምዕመናን ዕድገት የኋልዮሽ እየሄደ መሆኑን የጠቆሙት ፓትርያርኩ፣ ‹‹ዕድገቱ የኋልዮሽ መሆኑን የሚያውቅ ይኖር ይሆን? ችግሩንስ በሚገባ ተገንዝቦና በቁጭት ተነሳስቶ ችግሩን ለመቀልበስ የተደረገ ሙከራ አለ?›› የሚሉ ጥያቄዎቹን በማንሳት፣ እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚቆየው የሲኖዶስ ጉባዔ ምላሽ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ 

የኦርቶዶክሳውያን ተልዕኮ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ መሆኑን ሁሉም የዕምነቱ ተከታዮች፣ በተለይ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አባቶች እንደሚያውቁ የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ ከህሊና መቆርቆር እስከ ሕልፈተ ሕይወት የሚዘልቅ የመስዋዕትነት ዋጋ የሚጠይቅም መሆኑን መዘንጋት እንደሌለባቸው ለጉባዔው ተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡ 

ባህር አቋርጦ፣ ድንበር ተሻግሮ፣ እስከ ምድር ጽንፍ ተጉዞ፣ አስተምሮና ያላመነውን አሳምኖ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ማድረጉ ይቅርና በአገር ውስጥ ያሉትን ወገኖች፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሰባስቦ ምዕመናንን ማባዛት ብዙ እንዳልተሄደበት ፓትርያርኩ አስታውቀዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ትናንትና ስመ ክርስትና ሰጥታ በአባልነት የተቀበለቻቸው ልጆቿ፣ ዛሬ እናት ቤተ ክርስቲያናቸውን እየካዱ ወደ ሌላ ጎራ መቀላቀላቸው እየናረ መምጣቱን አክለዋል፡፡ 

‹‹ለመሆኑ ከቤተ ክርስቲያናችን እየወጡ ወደ ሌላ ካምፕ ለመሄድ ለምን መረጡ? የሚያስተምራቸው ካህን አጥተው? የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርተ ሃይማኖት ክፍተት ኖሮት? አስተዳደሩ የማያረካ ሆኖ? የካህን እጥረት? ወይስ ሌሎች ከእኛ የተሻሉ ሆነው ስለተገኙ ነው?›› የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሱት ፓትርያርኩ፣ መልሱን የጉባዔው ተሳታፊዎች የሚያውቁት ቢሆንም፣ ለሲኖዶሱ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ 

ቤተ ክርስቲያኗ ምዕመኗን የመጠበቅ ተልዕኮ እየተወጣች ባለመሆኗ ባዶዋን ከመቅረቷ በፊት፣ ለተደራጀና ድንበር የለሽ ትምህርተ ወንጌል መነሳት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደራዊ ሥራ ለምዕመናን ኅሊና እንቅፋት እየሆነ መሆኑን የገለጹት ፓትርያርኩ የሃይማኖቱን መርህ ጠብቀው፣ አስተዳደሩ የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠ፣ ግልጽ፣ ተዓማኒና ተጠያቂነትን ያሰፈነ፣ የምዕመናንን ልብ የሚያረካ ሥራ መሥራት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

በመጨረሻው የሕዝብና ቤት ቆጠራ አሥር በመቶ ምዕመናን ቁጥር መቀነሱ የታወቀ መሆኑን፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ አበ እምኔት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ፣ በየገዳማቱ የሚኖሩ መነኮሳትና ሌሎች በድጋሚ ቆጠራ የተደረገላቸው ቢሆንም፣ እንዳልተካተተና ለምዕመናኑ ቁጥር መቀነስም ሌላው ምክንያት መሆኑንም የሰበካ ጉባዔ ማደራጃ መምርያ ዋና ኃላፊ ሊቀ ማዕምራን ፋንታሁን ሙጨ ተናግረዋል፡፡ ለምዕመናን ትምህርተ ወንጌልን በማዳረስ አማኙን ለማብዛት እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት መምርያ ኃላፊው፣ በጋምቤላ ክልል በራሳቸው ቋንቋ ወንጌልን በማዳረስ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ከፍተኛ ኃላፊዎችን የሃይማኖቱ አባላት ማድረግ መቻሉን አክለዋል፡፡ 

ሙስናንና ብልሹ አሠራሮችን ለማስወገድ ቤተ ክርስቲያኗ ጠንክራ እየሠራች መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ትልቅ ሙስና ይፈጸምበታል የሚባለው የቤተ ክርስቲያኗ ሰፋፊ መሬት ጥናት ተደርጐበት መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት የሚመደቡ አስተዳዳሪዎች ጥፋት ፈጽመው ሲገኙ፣ ከአንዱ ቤተ ክርስቲያን ተነስተው ወደ ሌላ መዘዋወራቸው ቀርቶ ሙሉ በሙሉ የሚባረሩበት፣ በዘር፣ በመግባባትና ያለችሎታ የሚመደቡበት አሠራር ቀርቶ፣ በዕምነቱ ጥንካሬ፣ በላቀ ዕውቀት ምዕመናኑን በአግባቡ ሊያስተምር የሚችል የታመነበት አስተዳዳሪ የሚሾምበት አሠራር መዘርጋቱን የመምርያ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡         

 


መንግሥት አራት አዳዲስ ኮርፖሬሽኖች እንዲቋቋሙ መመርያ ሰጠ

$
0
0

እንደ አዲስ እንዲቋቋሙ መንግሥት ውሳኔ ከሰጠባቸው ስድስት ኮርፖሬሽኖች በተጨማሪ፣ ሌሎች አራት ኮርፖሬሽኖች እንዲደራጁ አቅጣጫ መሰጠቱን ምንጮች ገለጹ፡፡ 

የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን፣ የዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን፣ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ማዕድንና ጋዝ ምርቶች አቅርቦት ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ የማዕድን ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን እንዲቋቋሙ በመወሰኑ ኮርፖሬሽኖቹ ራሳቸውን እያደራጁ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ይዞ ኮርፖሬሽን ሆኖ የሚደራጀው የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን፣ በቀጥታ ተጠሪነቱ ለማን እንደሆነ እስካሁን ውሳኔ አልተሰጠም፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት መካከል አራቱ ኮርፖሬሽኖች፣ ተጠሪነታቸው በቀጥታ አዲስ ለተቋቋመው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ይሆናል፡፡

ከእነዚህ ስድስት ኮርፖሬሽኖች በተጨማሪ በቀጣዮቹ ወራት በአዲስ መልክ እንዲቋቋሙ መንግሥት አቅጣጫ የሰጠባቸው የተገጣጣሚ ሕንፃ አካላት ኮርፖሬሽን፣ የምግብ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ የባዮፊውል ኮርፖሬሽንና የመሬት ልማት ኮርፖሬሽን መሆናቸው ታውቋል፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደ ስብሰባ ላይ፣ የተገጣጣሚ ሕንፃ አካላት ድርጅት ያለበት ዕዳ ተሰርዞ እንደ አዲስ ኮርፖሬሽን ሆኖ እንደሚቋቋም መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ኮርፖሬሽን ቀደም ሲል ከሚያከናውነው ሥራ በተጨማሪ፣ ለመስኮትና በር የሚሆኑ የፒቪሲና አሳንሰር (ሊፍት) ምርቶችን እንዲያካትት በስብሰባው ላይ ተገኝተው ለነበሩ የተገጣጣሚ የሕንፃ አካላት ድርጅት ኃላፊዎች አቶ መኩሪያ መመርያ ሰጥተዋል፡፡

ባለፈው ሰሞን በሸራተን አዲስ በተካሄደ ስብሰባ ላይም አቶ መኩሪያ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በመሬት ልማት ላይ የሚሠራ የመሬት አቅርቦት ኮርፖሬሽን እንደሚቋቋም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ይህ የመሬት አቅርቦት ኮርፖሬሽን የሚያከናውናቸው ተግባራት ለጊዜው ግልጽ መሆን አልቻሉም፡፡ የመሬት ሥሪት ባለሙያዎችም የመሬት ኮርፖሬሽን ምን ሊሠራ እንደሚችል ግልጽ እንዳልሆነላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው ተጠባቂ የባዮፊውል ኮርፖሬሽን ነው፡፡ መንግሥት ባለፉት ሰባት ዓመታት ከተፈጥሮ ነዳጅ ጥገኝነት በከፊልም ቢሆን ለመላቀቅ ለባዮፊውል ልማት ትኩረት አድርጎ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በሚያካሂዳቸው የስኳር ፋብሪካዎች በርካታ መጠን ያለው ኢታኖል ማምረት ጀምሯል፡፡ ነገር ግን ለግል ኩባንያዎች ለጃትሮፋና ጉሎ ተከል የሚሆን ሰፋፊ መሬት ቢቀርብም፣ ኩባንያዎቹ ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ይህንን ዘርፍ በሚገባ እንዲመራና የባዮፊውል ኮርፖሬሽን እንዲቋቋም መንግሥት መመርያ መስጠቱን የሚናገሩት ምንጮች፣ ይህ ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ ከውጭ የሚገባውን ነዳጅ የመተካት ሚና ተሰጥቶታል፡፡

በሌላ በኩል የምግብ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ይቋቋማል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህ ኮርፖሬሽን ዘይትን የመሳሰሉ ስትራቴጂካዊ የምግብ ምርቶች ላይ በሰፊው ይሰማራል ተብሏል፡፡ እነዚህ ኮርፖሬሽኖች ተጠሪነታቸው አዲስ ለተቋቋመው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር እንደሚሆን ተመልክቷል፡፡

ሚኒስቴሩ ከእነዚህ አዳዲስ ኮርፖሬሽኖች በተጨማሪ ቀደም ሲል የተቋቋሙት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽንና የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንን በቀጥታ ያስተዳድራል፡፡ ከነዚህ ውጪ ያሉትን ብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ፓርክ ኮርፖሬሽንና አዲስ የተቋቋመው የኤሌክትሪክ ኮሬፖሬሽን የኮርፖሬት ገቨርናንስና ፋይናንስ ጤንነታቸውን እንዲከታተል ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ 

 

 

በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣን ማረሚያ ቤት ወረዱ

$
0
0

-ዓቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠርት ቀን ተቆርጦለታል 

ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ከፍተኛ የሆነ ጉቦ በመቀበል አገራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ከቀረጥ ነፃ ተሽከርካሪዎችን በማስገባት፣ በዘመዶቻቸውና በጓደኞቻቸው ስም ሀብት በማስቀመጥ፣ እንዲሁም ለመንግሥት መግባት የነበረበትን

ታክስና ቀረጥ ለግላቸው በማድረግ ከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ ወንድሙ ቢራቱ፣ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን የሰጠው፣ በተጠርጣሪው ላይ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ምርመራውን ማጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ ነው፡፡ ቡድኑ ምርመራውን ጨርሶ ለዓቃቤ ሕግ ማስተላለፉን ገልጾ፣ ዓቃቤ ሕግ አቶ ወንድሙን ጨምሮ በአራት ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ለመመሥረት የሚያስችለውን በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 109 (1) መሠረት የ15 ቀናት ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የአቶ ወንድሙ ጠበቃ የተጠየቀውን ጊዜ በመቃወም፣ ደንበኛቸው ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀው ነበር፡፡ ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪውን ዋስትና በሚያስከለክል ወይም በማይከለክል አንቀጽ ስለመክሰሱ ማወቅ እንደማይቻል ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ የዋስትናውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡  

በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ በአቶ ወንድሙና በሦስት ተጠርጣሪዎች ላይ ጥቅምት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ክስ እንዲያቀርብ ታዟል፡፡ 

 

ፍትሕን በብሔር ግንኙነት የሚሸጡና ለወሲብ ድርድር የሚያቀርቡ ሙያተኞች እንዳሉ ተነገረ

$
0
0
ፍትሕን በብሔር ግንኙነት የሚሸጡና ለወሲብ ድርድር የሚያቀርቡ ሙያተኞች እንዳሉ ተነገረ

-ከፖሊስና ከማረሚያ ቤት በበለጠ ፍርድ ቤት ለሙስና የተጋለጠ መሆኑ ተጠቆመ

በኢትዮጵያ የፍትሕ ተቋማት ውስጥ ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን ጠብቀው ሕዝባዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ታማኝ የፍትሕ ባለሙያዎች ያሉትን ያህል፣ ፍትሕን በገንዘብ የሚቸበችቡ፣ የተሰጣቸውን የሙያ ሥነ ምግባር ዘንግተው ዳኝነትና

ፍትሕን በአገር ልጅነት ወይም በብሔር ግንኙነት የሚሸጡና ለወሲብ ድርድር የሚያቀርቡ እንዳሉ ተነገረ፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን፣ ጥቅምት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ‹‹በኢትዮጵያ ፍትሕ ዘርፍ ሙስናን ለመከላከል የሚያስችሉ፣ የፍትሕ ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥና አፈጻጸም አመላካቾች›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ እንደተናገሩት፣ የተወሰኑ በፍትሕ ተቋማት ውስጥ ያሉ ሙያተኞች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ የሚገኙና ሙስና የሚፈጽሙ ናቸው፡፡ ሙስና በተንሰራፋበት በፍትሕ መድረክ ላይ ዜጐች በእኩልነት አይስተናገዱም፡፡ በተለይም ለነፃ ገበያ ዋነኛ መሠረት የሆነው የኮንትራት አስተዳደር ከቅጥፈት፣ ከአድልዎና ከአላስፈላጊ ባህሪዎች ነፃ ሆኖ ዳኝነት መስጠት በማይቻለበት ሁኔታ፣ አገሪቱ የምትመኘውን የኢኮኖሚ ዕድገትና የሚታሰበውን ያህል ኢንቨስተሮችን መሳብ እንደማይቻል ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡ ይኼንን እውነታም ሕዝቡ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው አክለዋል፡፡

ሙስናን የመታገያው የመጨረሻው መተማመኛ ተቋም የፍትሕ ሥርዓቱ በሙስና ከተፍረከረከ፣ አጠቃላይ የፀረ ሙስና ትግሉ አደጋ ላይ መውደቁ የማይቀር መሆኑን አቶ ዓሊ አስረድተዋል፡፡ የፍትሕ ተቋማት ከዘርፈ ብዙ የሙስና ዓይነቶች ካልፀዱ፣ አሠራራቸው ለሕዝብ ግልጽ ካልሆነ፣ በሕግ ከተቀመጠው የአሠራር ሥርዓት ያፈነገጡ በሕግ ተጠያቂ ካልሆኑ፣ ችግሩ በፍትሕ ተቋማት ብቻ እንደማይፈታና ወደ አገራዊ አደጋ እንደሚሸጋገር ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነሩ እንዳሉት፣ ሕግ መተርጐም ለዳኞች የተሰጠ ኃላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን ዳኞች ሕግን በነፃነት እንዳይተረጉሙ ለሕዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል የግል ፍላጐትን ለማሟላት በዳኝነት ሥራ ላይ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት ሊወገድ ይገባል፡፡ የኮሚሽነር ዓሊን ንግግር ተከትሎ በፍትሕና ሕግ ሥርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት ባልደረቦች ከላይ በተገለጸው ርዕስ ያዘጋጁትን ጥናት አቅርበዋል፡፡ 

ወ/ሪት ማዕረግ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ አሮን ደጐልና ዶ/ር ደጀኔ ግርማ የተባሉት የጥናቱ አቅራቢዎች፣ ጥናታቸውን ያደረጉት ለሙስና ዋና ተጋላጭ ናቸው ባሏቸው ፍርድ ቤት፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ፖሊስና ማረሚያ ቤቶች ላይ ነው፡፡ ጥናቱ ከድሬዳዋ ውጪ በቆዳ ስፋታቸውና በሕዝብ ብዛታቸው ቀዳሚ ናቸው ያሏቸውን ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች፣ ውስጥ ያሉ ዋና ዋና የፍትሕ አካላትን ማካተታቸውን አስረድተዋል፡፡

ዋና ዋና ያሉዋቸው አራቱ የፍትሕ አካላት ሊፈጽሟቸው የሚችሉ የሙስና ድርጊቶች ጉቦ፣ ሥራን መበደል፣ ምዝበራ፣ በሥልጣን መነገድና የማይገባ ሀብት ማካበት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ የፍትሕ አካላቱ ለሙስና ተጋላጭ የሚያደርጓቸው ምክንያቶች ዕውቀትና ክህሎት ማነስ፣ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ማነስ፣ ነፃና ገለልተኛ አለመሆን፣ ሰፊ ሥልጣን መኖር፣ ግልጽ የሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት አለመኖር በዋናነት የገለጿቸው ናቸው፡፡

ከወንጀለኞች ጋር በቅርበት መሥራት፣ ለኃላፊዎች ያላቸው መታየት ዝቅተኛ መሆን፣ ወንድማማችነት (ጥፋትን መሸፋፈን)፣ ተግባራቸው ለሕዝብ ግልጽ አለመሆን፣ ፖሊሶችን ለሙስና ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የማረሚያ ቤቶች ጥበት፣ በታራሚዎች አያያዝ ላይ የሠራተኞቹ ግንዛቤ አናሳ መሆን፣ የማረሚያ ቤት ሠራተኞች ለሕግ ተገዢ አለመሆን፣ የጥበቃ ሠራተኞች ከታራሚዎች ጋር የሚፈጥሩት ከሙያ ውጪ የሆነ ቅርበትና ወዳጅነት ደግሞ ማረሚያ ቤትን ለሙስና ተጋላጭ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ጥቂቶቹ መሆናቸውን ጥናት አቅራቢዎቹ ገልጸዋል፡፡ 

የፍርድ ቤትን አሠራር ቀልጣፋ ማድረግ፣ የፍርድ ቤት ሠራተኞችን ሥነ ምግባር ማሻሻል፣ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ ግልጽ አሠራር ማጐልበት፣ የዳኝነትን ነፃነት ማረጋገጥ፣ ከገቢ ጋር ተያያዢነት ያላቸውን ለሙስና የሚያጋልጡ ምክንያቶችን ማስወገድ፣ ተቋማትን ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች ማደራጀት፣ የመረጃና የሰነድ አያያዝ ሥርዓት ማጠናከር፣ የክትትል ሥርዓት መዘርጋት፣ የጥቅም ግጭት ማስወገድና ሌሎችንም ለሙስና በር የሚከፍቱ ምክንያቶች በጥናቱ መለየታቸውን አቅራቢዎቹ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ 

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ የፌደራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የዓቃቤ ሕግና የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች የቀረበውን ጥናት አድንቀው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡   

 

የስዊዘርላንድ ፕሬዚዳንት ማክሰኞ በፓርላማ ንግግር ያደርጋሉ

$
0
0
ፕሬዚዳንት ሲሞኔታ ሶማሩጋ

ለአራት ቀናት የሥራ ጉብኝት ባለፈው ቅዳሜ አዲስ አበባ የገቡት የስዊዘርላንድ ፕሬዚዳንት፣ የፊታችን ማክሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በፓርላማ ተገኝተው ንግግር እንደሚያደርጉ ተጠቆመ፡፡

ፕሬዚዳንት ሲሞኔታ ሶማሩጋ ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ጋር በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ ይመክራሉ ተብሏል፡፡ ማክሰኞ ከቀትር በኋላ በፓርላማ በመገኘት በሚያደርጉት ንግግርም ስዊዘርላንድ በፌዴራል ሥርዓት ያላትን ምርጥ ተሞክሮ ያካፍላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፕሬዚዳንቷ ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በማቅናትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የስደተኞች ኮሚሽን የሚያስተዳደረውን የስደተኞች ካምፕ እንደሚጎበኙ፣ በመቀጠልም በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ንግግር እንደሚያደርጉ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ፕሬዚዳንቷ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ከዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ጋር እንደሚወያዩም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የውጭ ኩባንያዎች ባልተጠናቀቀው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የማምረቻ ቦታ መያዝ ጀምሩ

$
0
0

-    45 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት የህንዱ ልብስ ፋብሪካ ሥራ ጀምሯል

በመጪው ሚያዝያ ሊጠናቀቅ እንደሚችል በሚነገርለት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የውጭ ኩባንያዎች የማምረቻ ቦታ መያዝ ጀመሩ፡፡ የቻይናው ኢንዶቻይን ኩባንያ ሁለት የማምረቻ ሼዶችን ለመከራየት ጫፍ ደርሷል፡፡

ኢንዶቻይን አፓረል የተባለው የቻይና ኩባንያ በሐዋሳ እየተገነባ በሚገኘው ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለ11 ሺሕ ካሬ ሜትር የማምረቻ ቦታ ማግኘቱን፣ የኩባንያው ጊዜያዊ ኃላፊ አኒላ ኩራላንቴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ኩባንያው ዝቅተኛውን 200 ሺሕ ዶላር ካፒታል በብሔራዊ ባንክ በኩል በመክፈል ወደ ኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተቀላቅሏል፡፡

ይሁንና ኩባንያው ተጨማሪ አምስት ሺሕ ካሬ ሜትር ማምረቻ እንዲሰጠው ድርድር ላይ እንደሚገኝ ያስታወቁት ኩራላንቴ፣ ስምምነት እስከሚፈጸም ድረስ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት እንደሚቆጠቡ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ፋብሪካው አልባሳትን የማምረት፣ የማቅለምና የላውንድሪ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችሉትን ማምረቻዎችን እንደሚተክል ገልጸው፣ ከ2,000 እስከ 3,000 ለሚገመቱ ዜጎች የሥራ ዕድል ሊያስገኝ እንደሚችልም አስታውቀዋል፡፡ ከ90 ከመቶ በላይ ሥራው የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችን ከሌሎች አምራቾች በመግዛት ማከፋፈል የሆነው ኢንዶቻይን ኩባንያ፣ ይህም ሆኖ ከቻይና ባሻገር በካምቦዲያና በቬትናም ማምረቻ ፋብሪካዎች እንዳሉት ኩራላንቴ ጠቅሰዋል፡፡

በመጀመሪያ የግንባታ ምዕራፉ በ100 ሔክታር መሬት ላይ ግንባታው እየተካሄደ ከሚገኘው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ በድሬዳዋ፣ በኮምቦልቻ፣ በመቀሌ፣ በአዳማና በጅማ ሌሎች ፓርኮች እንደሚገነቡና ለኢንቨስተሮች ዝግጁ እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩል በ45 ሚሊዮን ዶላር በቢሾፍቱ ከተማ የተገነባው የህንዱ ካኖሪያ አፍሪካ ቴክስታይልስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ጥቅምት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በተደረገ ሥነ ሥርዓት በይፋ ሥራ መጀመሩን አብስሯል፡፡ ኩባንያው ሥራ ከጀመሩ ትልልቅ አልባሳት ገዥዎች ምርቱን እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ለሪፖርተር የገለጹት የኩባንያው የገበያ ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ጃይ ሶያንታር ናቸው፡፡

ካኖሪያ በአብዛኛው የጅንስ ጨርቆችን በማምረት ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ሲጠበቅ ከወዲሁ ፒቪኤች፣ ቪኤፍ ኮርፖሬሽን እንዲሁም ጄ.ሲ. ፔሪ የተባሉ የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች ለመግዛት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ሶያንታር አስታውቀዋል፡፡ በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ሜትር በላይ የጅንስና የሌሎች አልባሳት ጨርቆችን በማምረት ለገበያ የማቅረብ አቅም ያለው ፋብሪካ መሆኑም ተነግሮለታል፡፡ 

የኤርፖርቶች ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ጨምሮ 15 ሠራተኞች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ተከሰሱ

$
0
0

-    በክሱ ባልና ሚስት ተካተዋል


የሙስና ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩት የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ጨምሮ 15 ሠራተኞች ላይ፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ክስ መሠረተባቸው፡፡

በፌዴራል በከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች፣ አቶ ማስረሻ ምትኩ ፈንቴ የድርጅቱ የሰው ኃይል ልማትና ማኔጅመንት ዳይሬክተር፣ አቶ አስቻለው አወቀ የስትራቴጂክ ፕላኒንግና ፋይናንስ ዳይሬክተር፣ አቶ ፍቅረ ማርያም አያሌው የሰው ኃይል አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ ጌታቸው ደበበ የፋይናንስ ኦፊሰር፣ የአቶ ጌታቸው ባለቤት ወ/ሮ ስሜነሽ ጌታቸው አበጋዝ (የግል ሠራተኛ)፣ መቅደላዊት ባንቱ የወ/ሮ ስሜነሽ ወንድም ሚስት፣ ወ/ሮ ገነት አረጋ የአቶ ጌታቸው እናት፣ አቶ ሚካኤል አበበ የድርጅቱ የፋይናንስ አገልግሎት የክፍያና የሒሳብ ማጠቃለያ ማስተባበሪያ ኃላፊ፣ አቶ ንጉሤ ካህሳይ የፋይናንስ ኦፊሰር፣ እፀገነት ብርሃኑ ከፍተኛ የሒሳብ ሠራተኛ፣ ሔለን ብርሃነ የከፍተኛ ጥቅማ ጥቅምና መረጃ ኦፊሰር፣ አቶ መላኩ ወርቅነህ የፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊ፣ እሌኒ ኤልያስ የፋሲሊቲዎች ዳይሬክቶሬት ኦፊስ ኢንጂነር የነበረች፣ አቶ ዘነበ ወሰኔ የራንዌይ ቴክኒሻን የነበረና አቶ መልካሙ አበበ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አስተዳደር ጀማሪ የፋይናንስ ኦፊሰር ናቸው፡፡

ባልና ሚስት የሆኑት አቶ ጌታቸውና ወ/ሮ ስሜነሽ በመመሳጠር ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያለውን የሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ክፍያዎች አገልግሎት ውልን በመጠቀም፣ ሠራተኞች ባልሆኑ 189 ሰዎች ስም በድምሩ 3,335,950 ብር ወደ ግል አካውንታቸው ማስገባታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

ተከሳሾቹ የሐምሌና የነሐሴ ወር ደመወዝ ፔሮል በመሥራትና በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ ኃላፊዎችን በማስፀደቅ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤርፖርቶች ቅርንጫፍ ከድርጅቱ ገንዘብ ላይ ተቀናሽ በማድረግ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጀሞ ቅርንጫፍ በወ/ሮ ስሜነሽ ስም በተከፈተ አካውንት ውስጥ ማስገባታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በግለሰቧ ስም ብቻ የተከፈተውን አካውንት (Joint and/or Account) በጥምረት በማድረግ ወደ አቢሲኒያ ባንክ ጀሞ ቅርንጫፍ ማዛወራቸውንም ክሱ ይተነትናል፡፡

አቶ ጌታቸው በድርጅቱ የሚከፈላቸው የተጣራ ደመወዝ 1,173 ብር የነበረ ቢሆንም ደመወዛቸውን ወደ 9,816 ብር ከፍ በማድረግ፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ያላግባብ በመጠቀም በመንግሥትና በድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

እሌኒ ኤልያስ የተባለች ተከሳሽ ድርጅቱን ከየካቲት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በራሷ ፈቃድ የለቀቀች መሆኗ እየታወቀ፣ አቶ ጌታቸው ከየካቲት እስከ ነሐሴ 2007 ዓ.ም. ድረስ በፔሮል ውስጥ በማካተት በወር 3,420 ብር በድምሩ 23,943 ብር እንዲከፈላት ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ አቶ ዘነበ ወሰኔ የተባለው ተከሳሽም ከአቶ ጌታቸው ጋር በመመሳጠር፣ ከታኅሳስ 1 እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ በወር 1,562 ብር በድምሩ 14,058 ብር እንዲከፈለው መደረጉም በክሱ ተጠቅሷል፡፡ አቶ ጌታቸው ለአቶ መልካሙ አበበ 13,178 ብር በባንክ ሒሳባቸው እንዲገባላቸው ማድረጋቸውንም ክሱ ያብራራል፡፡

አቶ ጌታቸውና ወ/ሮ ስሜነሽ ከድርጅቱ በተጭበረበረ መንገድ ወስደዋል የተባለውን ገንዘብ፣ በዘመዶቻቸውና በራሳቸው የተለያየ መጠን በማድረግ በባንክ በማስገባት፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስለው ማቅረባቸውን፣ እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29(2ሀናመ) ሥር የተደነገገውን መተላለፋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

አቶ ፍቅረ ማርያም፣ ማስረሻ፣ ሚካኤልና ንጉሤ የተባሉት ተከሳሾች ደግሞ በደመወዝ መክፈያ ፔሮልና መሸኛ ደብዳቤው ላይ የተገለጸው ደመወዝ ቀድሞ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ ፍፁም የተጋነነ ሆኖ እያለ፣ የሰነዱን ትክክለኛነት ሳያረጋግጡና ሳይፈትሹ በፊርማቸው በማፅደቃቸው በድርጅቱና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ክሱ ይዘረዝራል፡፡ እፀገነት ብርሃኑ፣ ሔለን ብርሃነ፣ አስቻለው አወቀና መላኩ ወርቅነህ የተባሉት ተከሳሾች ደግሞ፣ እሌኒ ኤልያስ የተባለችው ተከሳሽ ከድርጀቱ ከየካቲት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በራሷ ፈቃድ ሥራዋን መልቀቋን የካቲት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሰው ሀብት ልማትና ማኔጅመንት በደብዳቤ ካሳወቀች በኋላ፣ ያልሠራችበት ጊዜ ደመወዝ ተመላሽ እንዲሆን ማድረግ ሲገባቸው ሳያደርጉ በመቅረታቸው፣ ግለሰቧ 23,943 ብር ያላግባብ እንዲከፈላት በማድረጋቸውና ግዴታቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸውን ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ ተጠርጣሪ ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ያላግባብ ሥልጣን መጠቀም፣ የመንግሥትን ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሥራን በማያመች አኳኋን መምራት፣ በሙስና ወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ  የሚሉ አምስት የሙስና የወንጀል ክሶች ቀርበውባቸዋል፡፡

ክሱን የሚመረምረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ክሱን ካሰማ በኋላ፣ ተከሳሾቹ ዋስትና እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የአቶ ጌታቸው፣ ወ/ሮ ስሜነሽ፣ ወ/ሮ መቅደላዊትና ወ/ሮ ገነት አረጋን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ ሌሎቹ ተከሳሾች ከ8,000 ብር እስከ 15,000 ብር በሚደርስ ዋስ እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ለኅዳር 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጥሯል፡፡   

የቴክኒክ እክል የገጠመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድሪምላይነር አውሮፕላን በሰላም አረፈ

$
0
0
አየርላንድ ዳብሊን አውሮፕላን ማረፊያ በሰላም ያረፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድሪምላይነር አውሮፕላን

ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ማለዳ ከዳብሊን አየርላንድ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ በመብረር ላይ የነበረ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን፣ አንደኛው ሞተር ላይ በተፈጠረ የቴክኒክ ችግር ተመልሶ ዳብሊን ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በሰላም ማረፉ ተረጋግጧል፡፡

ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ በዳብሊን በኩል ወደ ዋሽንግተን ዳላስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ይበር የነበረው ድሪምላይነር አውሮፕላን፣ በዳብሊን አጭር ቆይታ ካደረገ በኋላ ከንጋቱ 12 ሰዓት ከዳብሊን ኤርፖርት በሰላም መነሳቱ ታውቋል፡፡ አውሮፕላኑ አንድ ሰዓት ያህል ከበረረ በኋላ ካሉት ሁለት ሞተሮች የግራ ክንፍ ላይ ያለው አንደኛው ሞተር የቴክኒክ ችግር ስለገጠመው፣ የአውሮፕላኑ አብራሪዎች ይህንኑ ለዳብሊን ኤርፖርት አሳውቀው በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ይበር የነበረውን አውሮፕላን ወደ ዳብሊን መልሰው በሰላም ማሳረፋቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በድረ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ የበረራ ቁጥር ‹‹ኢቲ 500›› የግራ ሞተር የቴክኒክ ችግር የገጠመው ቢሆንም፣ አብራሪዎቹ ዓለም አቀፍ የበረራ ደኅንነት መመርያዎችን በመከተል አውሮፕላኑ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስበት በሰላም ማሳረፋቸውን አስታውቋል፡፡

‹‹አብራሪዎቻችን ባሳዩት ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት አድናቆታችንን እንገልጻለን፤›› ያለው አየር መንገዱ፣ በአውሮፕላኑ ሞተር ላይ የተከሰተውን የቴክኒክ ችግር መንስዔ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የቴክኒክ ባለሙያዎችና የአውሮፕላኑ ሞተር አምራች የሆነው ጄኔራል ኤሌክትሪክ ኢንጂነሮች በመመርመር ላይ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

የመንገደኞቹ ደኅንነትና ምቾት እንደሚያስጨንቀው የገለጸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለበረራ ቁጥር ኢቲ 500 መንገደኞች ሌላ አውሮፕላን በመላክ ጉዞዋቸውን በዕለቱ ወደ ዋሽንግተን እንዲቀጥሉ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 73 አውሮፕላኖች ባለቤት ሲሆን፣ አሥራ ሦስቱ ድሪምላይነር ናቸው፡፡ አየር መንገዱ ስድስት ተጨማሪ ድሪምላይነር አውሮፕላኖች ከቦይንግ ኩባንያ አዟል፡፡

የድሪምላይነር አውሮፕላኖች አገልግሎት መስጠት በጀመሩበት ወቅት (እ.ኤ.አ. 2012 – 2013) ከባትሪ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ችግር ገጥሟቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ አዲስ የአውሮፕላን ቴክኖሎጂ እስኪላመድ ድረስ አንዳንድ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ የሚገልጹት የአቪዬሽን ባለሙያዎች፣ የድሪምላይነር አውሮፕላን በነዳጅ ቁጠባና የበረራ ምቾት ወደር የማይገኝለት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም አየር መንገዳቸው እያንዳንዱን ድሪምላይነር አውሮፕላን በቀን በአማካይ 14 ሰዓት እንደሚያበር ገልጸው፣ በአውሮፕላኑ አጠቃላይ ብቃት መርካታቸውን በተደጋጋሚ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡


የውጭ ኩባንያዎችን በመኖርያ ቤቶች ግንባታ ለማሳተፍ የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

$
0
0

በአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ውስጥ የውጭ አገር ኮንትራክተሮችን ለማስገባት የወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ተገምግሞ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት፣ ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ተላከ፡፡

የጨረታውን ውጤት ሚኒስቴሩ የሚቀበል ከሆነ፣ 14 የውጭ ኩባንያዎች በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በተከፈተው ዓለም አቀፍ ጨረታ 28 የውጭ አገር ኩባንያዎች ፕሮፖዛላቸውን ይዘው በመቅረብ ተወዳድረው ነበር፡፡

ላለፉት ዘጠኝ ወራት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ኢንስቲትዩት ጨረታውን በተመለከተና የውጭ ኩባንያዎች በመኖርያ ቤት ግንባታ ውስጥ ሲሳተፉ የመጀመርያ ጊዜ በመሆኑ አሠራሩን ሲያጠና ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሴፍ ብሩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢንስቲትዩቱ ሥር የተዋቀረው ኮሚቴ ሥራውን ጨርሶ ለሚኒስቴሩ ልኳል፡፡

በግምገማ ሒደቱ በክፍያ ላይ መግባባት ላይ ያለመደረሱን ዶ/ር ዮሴፍ አስረድተው፣ የውጭ ኩባንያዎቹ ከራሳቸው የፋይናንስ ምንጭ ይዘው ይመጣሉ? ከመጡስ እንዴት ነው የሚከፈለው? መንግሥትስ በምን ዓይነት መንገድ ክፍያ ይፈጽማል? ክፍያ የሚፈጸመው በውጭ ምንዛሪ ከሆነ በአገሪቱ ላይ የምንዛሪ እጥረት አይፈጠርም ወይ? በሚሉት ጉዳዮች ኮሚቴው የጠራ አቋም አለመያዙን አስረድተዋል፡፡
 
የውጭ ኮንትራክተሮችን ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ በመኖርያ ቤቶች ግንባታ ለማሰማራት የአገሪቱ ሕጎች የማይፈቅዱ መሆናቸው ተዘርዝሯል፡፡ ሚኒስቴሩ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የኮንስትራክሽን ግዢ የሚፈጽምበት ረቂቅ ሕግ ማዘጋጀቱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ዶ/ር ዮሴፍ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ከእነዚህ አማራጮች በተጨማሪ ኢንስቲትዩቱ ሌሎች የመኖርያ ቤቶች ግንባታ አማራጮችን ለማየት እየሞከረ ነው፡፡
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በቀረበለት ፕሮፖዛል ላይ ውሳኔ ከሰጠ፣ በዚህ ዓመት 14 የውጭ ኩባንያዎች 100 ሺሕ የሚጠጉ መኖርያ ቤቶች በአዲስ አበባ ከተማ እንዲገነቡ ይደረጋሉ ተብሏል፡፡ ኩባንያዎቹም የቤቶቹን ግንባታ በ18 ወራት እንደሚፈጽሙ ታምኗል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2007 ዓ.ም. ተጀምረው ያልተጠናቀቁ 50 ሺሕ ቤቶችን ጨምሮ፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 250 ሺሕ ቤቶችን የመገንባት ዕቅድ አውጥቷል፡፡

እስካሁን በአገር ውስጥ ኩባንያዎች አቅም እየተካሄደ ያለው የቤቶች ግንባታ በሚፈለገው ፍጥነት እየተካሄደና ለተጠቃሚው እየተላለፈ ባለመሆኑ ነዋሪዎች ቅሬታ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ መንግሥት የመኖርያ ቤቶች ግንባታ በአስቸኳይ ተካሂዶ ለኅብረተሰቡ መተላለፍ አለበት የሚል አቋም በመያዝ ለውጭ ኩባንያዎች በሩን ክፍት ማድረጉ በአዎንታዊ ጎኑ እየታየ ነው፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌም በቅርብ እንደተናገሩት፣ በተያዘው በጀት ዓመት የውጭ ኩባንያዎች በቤቶች ግንባታ እንዲሰማሩ ይደረጋል፡፡

ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ የታሰሩት የምክር ቤት አባል ጉዳይ አከራከረ

$
0
0


ከስምንት ወራት በፊት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት የጋምቤላ ክልል ምክር ቤትና ክልሉን በመወከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ አሽኔ አስቲን ቲቶይክ በእስር ላይ የሚገኙት፣ ያለመታሰር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተጥሶ መሆኑ በፍርድ ቤት አከራከረ፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ነሐሴ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ጽፎ ያቀረበውን ክስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ጥቅምት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ለተከሳሹ በንባብ ሊያሰማ የነበረ ቢሆንም፣ ጠበቃቸው አቶ አመሐ መኮንን ተቃውመዋል፡፡ ጠበቃው ተቃውሞአቸውን በሚመለከት ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ደንበኛቸው አቶ አሽኔ አስቲን ቲቶይክ ላለፉት ስምንት ወራት በእስር ላይ የሚገኙት የጋምቤላ ክልል ምክር ቤትና ክልሉን በመወከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሆኑና ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ነው፡፡

የክልሉ ሕገ መንግሥትም ሆነ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የምክር ቤት ተመራጭ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ሊከሰስም ሆነ ሊታሰር እንደማይችል ደንግጎ ሳለ፣ ደንበኛቸው ታስረው መክረማቸው ሕገ መንግሥቱን መጣስ መሆኑን ጠበቃው አስረድተዋል፡፡ የተሰጣቸውን የምክር ቤት አባልነት መታወቂያም አለመመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በዕለቱ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ እንዳስረዳው፣ ተከሳሹ የምክር ቤት አባል መሆናቸው እርግጥ ቢሆንም አሁን ግን የምክር ቤት አባል አለመሆናቸውን ገልጿል፡፡ የምክር ቤት አባልነት መታወቂያ የወሰዱትም በ2003 ዓ.ም. መሆኑን ጠቅሶ ጊዜው ማለፉን አስረድቷል፡፡ አባል ስላለመሆናቸውም ማስረጃ ማቅረብ እንደሚችል ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱም የዓቃቤ ሕግን ማስረጃ ለመጠባበቅ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

አቶ አሽኔ አስቲን ቲቶይክ፣ አቶ አሞት አጉዋ አኳሞይና አቶ ጀማል ዑመር የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(2)ን በመተላለፍ የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) ቡድን ውስጥ መሥራችና አባል በመሆን፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፈራረስና የጋምቤላ ክልልን ከፌዴሬሽን ለመገንጠል ሲቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል ክስ እንደተመሠረተባቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ቡድኑ ኬንያ ናይሮቢ በሚያደርገው ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ሊሄዱ ሲሉ መጋቢት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንደነበረ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡


አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደሌሉ አስተዳደሩ ገለጸ

$
0
0
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ

-    ተከሳሾቹ እሳቸው የማይቀርቡ ከሆነ ብይን ይሰጠን አሉ

 በተደጋጋሚ ለሦስት ጊዜያት በተጠሩበት የመከላከያ ምስክርነት ያልቀረቡበትን ምክንያት ለጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓም. እንዲያቀርብ የታዘዘው የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደሌሉ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በላከው ደብዳቤ አስታወቀ፡፡

በእነ ዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ የተከሰሱት አቶ አሸናፊ አካሉ፣ አቶ ደህናሁን ቤዛ፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁንና አቶ አንሙት የኔዋስ፣ አቶ አንዳርጋቸውን በመከላከያ ምስክርነት እንደሚፈልጓቸው ለፍርድ ቤት አመልክተው ነበር፡፡ ከየመን በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው መምጣታቸውን በመጠቆም፣ ዋናው ክሳቸው በኤርትራ ከእሳቸው ጋር በመገናኘት መመርያና ትዕዛዝ ስለመቀበላቸው መሆኑን አስታውሰው እንዲያስረዱላቸው መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን ዓቃቤ ሕግ አቶ አንዳርጋቸው የዕድሜ ልክ እስራትና ሞት የተፈረደባቸው በመሆኑ፣ ቀርበው ሊመሰክሩ አይገባም በማለት ተቃውሞ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱም የዓቃቤ ሕግን ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ ጥያቄውን ተቀብሎ ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር፡፡

ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. አቶ አንዳርጋቸው ይቀርባሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ማረሚያ ቤቱ በላከው ደብዳቤ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት አለመኖራቸውን በመግለጹ ተከሳሾቹ ብሶታቸውን ገልጸዋል፡፡ ማረሚያ ቤቱ ቀደም ያሉት ትዕዛዞች በትክክለኛ አድራሻ እንዳልተጻፉለት በመግለጽ ሲያመላልሳቸው ከርሞ፣ መጨረሻ ላይ እንደሌሉ መግለጹ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ክሳቸውን መከላከል ከጀመሩ ከአንድ ዓመት በላይ ማስቆጠራቸውንና በማረሚያ ቤት በደል እየደረሰባቸው ከመሆኑ አንፃር የአስተዳደሩ መልስ የማይታመን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዕድሜ ልክና የሞት ፍርደኛ ከማረሚያ ቤት ውጪ ሊታሰር እንደማይችል የገለጹት ተከሳሾቹ፣ አቶ አንዳርጋቸው ከየመን ተይዘው እንደመጡ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይልና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌቪዥን መናገራቸውን በመጥቀስ በወቅቱ ለሁለቱም አካላት ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው ለፍርድ ቤቱ ማመልከታቸውን አስታውሰዋል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በመከላከያ ምስክርነት እንዳይሰሙ ማረሚያ ቤት ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የእሳቸው ምስክርነት ቀርቶ ብይን እንዲጣቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ተከሳሽ ምንዳዬ ጥላሁን የተባለው ተጠርጣሪ ግን፣ ‹‹ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር ተገናኝተህ መመርያ ተቀብለሀል ስለተባልኩ ቀርበው መመስከር አለባቸው፤›› በማለት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን አቤቱታ ካዳመጠ በኋላ አቶ አንዳርጋቸው ይገኙበታል ለተባለው ተቋም ትዕዛዝ ለመስጠት፣ ለጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡


በቃል ትዕዛዝ ብቻ በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ ግዥ እየተፈጸመ ነው

$
0
0

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ከሕግ ውጪ፣ በቃል በሚሰጥ ትዕዛዝ ብቻ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጭ በማድረግ ግዥ እየፈጸመ መሆኑ ታወቀ፡፡

የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥቆማ ደርሶት ምርመራ በመጀመር መረጃዎችን እያጠናቀረ መሆኑ ታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የግዥ መመርያ ከ500 ሺሕ ብር በላይ ወጪ የሚደረግ ከሆነ፣ በውስን ጨረታ ግዥ መፈጸም ይከለክላል፡፡ ነገር ግን የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት ሲባል፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ውስን ጨረታዎችን እያወጣ በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ ግዥ ሲፈጽም መቆየቱ ታውቋል፡፡

ይህ ሕግን ያልተከተለ ግዥ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ትኩረት የሳበ በመሆኑ፣ ኮሚሽኑ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የፈጸማቸውን የተለያዩ ግዥዎች ለመመርመር መረጃ ጠይቆ ወስዷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለሚመራው ኮማንድ ፖስት ተጠሪ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራው የቤቶች ግንባታ ሥራ አመራር ቦርድ፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱን ሥራ በቅርብ እየተከታተለ መመርያ ይሰጣል፡፡

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ፣ በቃል በሚሰጥ ትዕዛዝ ብቻ ግዥ እየፈጸሙ መሆናቸውን በግልጽ ተናግረዋል፡፡

አቶ ይድነቃቸው እንዳሉት፣ የበላይ አመራሮች በቃል በሚሰጡት ትዕዛዝ ብቻ ከሕግ ውጪ ግዥ እየተፈጸመ ነው፡፡ በተጨማሪም የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት እየተመራ ያለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው ኮማንድ ፖስት፣ በምክትል ከንቲባውና ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ መሆኑን ገልጸው፣ በአብዛኛው በጽሑፍ ሳይሆን በቃል ትዕዛዝ መመርያ እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የሕግ ማዕቀፍ እንዲስተካከል ወይም ሰርኩላር እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ጠይቀናል፣ እስካሁን ምላሽ አላገኘንም፤›› ያሉት አቶ ይድነቃቸው፣ ‹‹የፀረ ሙስና ኮሚሽን ግዥ ስንፈጽም የቆየንባቸውን መረጃዎች ወስዷል፤›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 6.3 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ግዥ ፈጽሟል፡፡ ‹‹ያለምንም የጽሑፍ ትዕዛዝ አመራሮቻችንን አምነን በ1.6 ቢሊዮን ብር የአርማታ ብረት ግዥ አከናውነናል፤›› በማለት ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው አቶ ይድነቃቸው ሳይሸሽጉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ ይህንን ገንዘብ እያንቀሳቀስን የአዲስ አበባ የግዥ መመርያ ውስን ጨረታ ከ500 ሺሕ ብር በታች ነው ይላል፤›› በማለት የሕግ ማዕቀፉ ሊሻሻል እንደሚገባም አቶ ይድነቃቸው አሳስበዋል፡፡ 

ነገር ግን የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ግዥዎቹን ለመፈጸሙ በጽሑፍ ሰርኩላር እንዲወርድለት ቢጠይቅም፣ እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የፀረ ሙስና ኮሚሽን የተለያዩ ሰነዶችን በመውሰድ በግዥ አፈጻጸሙ ላይ ምርመራ ማካሄዱን ቀጥሏል፡፡


የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ ረቂቅ ደንብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀረበ

$
0
0

የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማስተካከያ ለማካሄድ የሚያስችለው የኢነርጂ ሥራዎች ረቂቅ ደንብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡

የግል ባለሀብቶች በኢነርጂ ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ቢፈልጉ የተከለከለ ባይሆንም፣ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ግን ዝቅተኛ በመሆኑ በዘርፉ ለመሰማራት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ዘገምተኛ ሆኖ መቆየቱ ይነገራል፡፡ 

በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የግል ባለሀብቶች በኤሌክትሪክ ማመንጨት ዘርፍ እንዲሰማሩ፣ መንግሥት የተለያዩ ማበረታቻዎችን እንደሚሰጥ ተጠቅሷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ከሆነ ለጋሾች ጋር በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኢነርጂ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ ኢንቨስተሮች ያሏቸው አገሮች ተወካዮች፣ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚገባና ማሻሻያው ከተደረገ በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጐት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሰጡት ምላሽ በውኃ፣ በጂኦተርማል፣ በፀሐይ፣ በንፋስና በመሳሰሉት ኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ማካሄድ ለሚፈልጉ ኢንቨስተሮች የመንግሥት በር ክፍት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዘርፉ የሚሰማሩትንም ባለሀብቶች መንግሥት እንደሚያበረታታ ተናግረዋል፡፡

በዋናነት የኢንቨስተሮች ትኩረት ግን የታሪፍ ማሻሻያው ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ሞገስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢነርጂ ሥራዎች ረቂቅ ደንብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ይህ ደንብ ስለኤሌክትሪክ ማመንጨት፣ ማስተላለፍ፣ ማከፋፈል፣ መሸጥ፣ ማስመጣት ወይም መላክ በጥልቀት ይተነትናል፡፡ በእርግጥ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ቁጥሮች ከዚህ ደንብ በኋላ በሚወጣው መመርያ የሚገለጹ ቢሆንም፣ አቶ ጌታሁን እንዳሉት ግን በመመርያው የሚወጣው ታሪፍ የኢንቨስትመንት ወጪን መሸፈን በሚያስችል ደረጃ የተቃኘ ነው፡፡

ኢነርጂ ለማመንጨት የሚሰጥ ቀነ ገደብ በረቂቅ ደንቡ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ ከውኃና ጂኦተርማል የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የተሰጠው የባለቤትነት ጊዜ 25 ዓመት ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ውጭ ለመላክም ሆነ ለማስመጣት የተሰጠው ፈቃድ ጊዜ ለአሥር ዓመት ነው፡፡

በእነዚህ ሕግጋት ወደ ኢንቨስትመንት የሚገቡ ባለሀብቶች የሚያመነጩትን የኤሌክትሪክ ኃይል በመመርያ በሚገለጸው ታሪፍ፣ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ይሸጣሉ፡፡ አቶ ጌታሁን እንዳሉት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ ደንቡን ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 


Viewing all 1779 articles
Browse latest View live