-ግብፅ የኢትዮጵያ ግድብ ቅርሶቼን ለአደጋ ያጋልጣል እያለች ነው
የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የጠራ አቋም መያዝ የተቸገሩት የግብፅ ባለሥልጣናት በግድቡ ላይ ምንም ዓይነት ውይይት እንደማያደርጉ ካሳወቁ በኋላ፣ ሐሳባቸውን በመቀየር ውይይት በመምረጣቸው ምክንያት በዚህ ሳምንት የግብፅ የውኃ ሀብት ሚኒስትር አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 4 ቀን 2014 በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውኃ ሚኒስትሮች የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ለሦስተኛ ጊዜ ለመምከር ቢገናኙም ውይይቱ ሳይስማሙ መበተኑ ይታወሳል፡፡ ከዚህ በኋላ ውይይት እንደበቃቸው በተደጋጋሚና በተለያዩ መንገዶች የግብፅ ባለሥልጣናት ቢናገሩም፣ የውኃ ሀብትና የመስኖ ሚኒስትሩ መሐመድ አብዱል ሙታሊብ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር ለመነጋገር ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ የግብፅ ሚኒስትር ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር ለመነጋገር ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ የጉብኝት ፈቃድ እንደተሰጣቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዚህ የጉብኝት ፈቃድ መሠረት በዚህ ሳምንት አዲስ አበባ በመምጣት ከሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትንም እንደሚያነጋግሩ ታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ የግብፅ ባለሥልጣናት የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ እያሳዩት የሚገኘው ተለዋዋጭ አቋም እንደበፊቱ ላለመቀጠሉ እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሰሞኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የግብፅ መንግሥት የህዳሴውን ግድብ ግንባታ በተመለከተ የተለያዩ ነጥቦችን በማንሳት ከኢትዮጵያና ከሱዳን መንግሥታት ጋር ለሦስት ጊዜያት ቢወያይም፣ በውይይቶቹ የግብፅን መንግሥት አቋም ለይቶ ማወቅ አለመቻሉን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ያስረዳሉ፡፡
በተለይ በውይይቱ የተሳተፉ የመንግሥት ተወካዮች የግብፅ መንግሥት በውይይት አማካይነት መግባባት ላይ ከመድረስ ይልቅ የተደበቀ አጀንዳ እንዳለው ይገምታሉ፡፡ ይህንን የግብፅ የተደበቀ አጀንዳ ከሚጠረጥሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮች መካከል አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ይገኙበታል፡፡ እንደሳቸው ገለጻ የግብፅ መንግሥት በህዳሴው ግድብ ላይ ያለውን ጥርት ያለ አቋም ማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምናልባትም በቅርቡ በግብፅ በፀደቀው አዲሱ ሕገ መንግሥት መሠረት የሚመሠረተው መንግሥት ይህንን ችግር ይፈታዋል ብለው ይገምታሉ፡፡
በአጠቃላይ ግብፅ የህዳሴውን ግድብም ሆነ ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከዚህ በኋላ ያላት ብቸኛ አማራጭ ከተፋሰሱ በተለይም ከላይኛው ተፋሰስ አገሮች ጋር መወያየት ብቻ ነው ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ውይይት ሲባልም እውነተኛ ወይይት መሆን አለበት፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
በሌላ በኩል የግብፅ የመረጃ አገልግሎት ‹‹የግብፅ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በአፍሪካ የገጠሙት ፈተናዎች›› በሚል ባደረገው ጥናት ያቀረባቸው ፈተናዎች በዋናነት የሚያጠነጥኑት በውኃ ፖለቲካ ላይ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ግብፅ የዓባይ ወንዝ ተጋሪ ከሆኑ የአፍሪካ አገሮች ማለትም ከኢትዮጵያ፣ ከኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ከታንዛኒያ፣ ከኬንያና ከብሩንዲ ፈተና ተጋርጦባታል ይላል፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ የግብፅ መንግሥት መከተል ይገባዋል በማለት ከሚያስቀምጣቸው የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል፣ ግብፅ ከዚህ ቀደም የዓባይ ውኃን አስመልክቶ ከምታንፀባርቀው አቋም የተለየና የውኃ መጋራትን መሠረት ያደረገ አቀራረብ መሆን ይገባዋል ይላል፡፡
በተጨማሪም የአፍሪካ አገሮች በተለይም የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ተማሪዎች በግብፅ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) እንዲያገኙ ማድረግና የባህል ማዕከላትን በተፋሰሱ አገሮች በመክፈት ግብፅን ከአፍሪካውያን ጋር ማቀራረብ ተገቢ ነው በማለት ያስረዳል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የግብፅ ጥንታዊ ቅርሶች ሚኒስትር መሐመድ ኢብራሂም ሰሞኑን የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በግብፅ ላይ ሊያመጣ ስለሚችለው ጥፋት የተለየ አዲስ ሐሳብ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ግድቡ የግብፅን የውኃ መጠን ስለሚቀንስ ለግብፅ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ መሆኑን ባለሥልጣናቱ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ የቅርስ ሚኒስትሩ ደግሞ በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ምክንያት የግብፅ ጥንታዊ ቅርሶች (ፒራሚዶችን ጨምሮ) ለአደጋ ያጋልጣቸዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዕውን መሆን የከርሰ ምድር ውኃ መጠንን በመቀነስ የመሬት አለመረጋጋት (መንሸራተትን) የሚፈጥር በመሆኑ፣ የግብፅ ጥንታዊ ቅርሶች አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ በማለት አዲስ ሐሳብ ይዘው ቀርበዋል፡፡
የግብፅ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር የሚገኙ ሲሆን፣ የአሁኑ በጥንታዊ ቅርሶች ላይ አደጋ ተደቅኗል የሚለው ሐሳባቸው ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ዴይሊ ኒውስ በተሰኘው ድረ ገጽ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን የግብፅ ባለሥልጣናትን ተለዋዋጭ አቋም አውግዘዋል፡፡ በዓባይ ወንዝ ፍትሐዊ ተጠቃነሚት ላይ ማተኮር ሲገባቸው ግድቡን በጠላትነት መመልከታቸው ተቀባይነት እንደሌለው በማስረዳት፣ አሁንም ለድርድርና ለውይይት ራሳቸውን ከማዘጋጀት ውጪ ሌላው ተግባራቸው ተቀባይነት እንደሌለው ነግረዋቸዋል፡፡
የግብፅ ባለሥልጣናት ለኢትዮጵያ ዕርዳታና ብድር በማስከልከል፣ የግድቡን ግንባታ ጉዳይ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለመውሰድ መነሳታቸው አልበቃ ብሎ፣ አንዴ የግንባታ መጠኑ እንዲቀንስ ሌላ ጊዜ ደግሞ በቅርሶች ላይ አደጋ ያደርሳል ማለታቸው ተወግዟል፡፡ ታላቁ የአስዋን ግድብ ሲገነባ ለምን ይህ ጥያቄ አልተነሳም በማለት የሞገቱት ኢትዮጵያውያን፣ ይህ ተለዋዋጭ የግብፅ ባለሥልጣናት አቋም አደብ እንዲገዛም ጠይቀዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት 45 አባላት ያሉት የዲፕሎማሲ ቡድን አዲስ አበባ ለመምጣት ከባለሥልጣናትና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመገናኘት ውይይት አድርጓል፡፡ አሁን ደግሞ የውኃ ሀብትና የመስኖ ሚኒስትሩ መሐመድ አብዱል ሙታሊብ አዲስ አበባ በመምጣት በግድቡ ላይ ለመነጋገር ጥያቄ አቅርበው ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ግብፆች ተለዋዋጭ በሆነው አቋማቸው እስከመቼ የተለያዩ ሐሳቦችን ያራምዳሉ የሚሉ የመስኩ ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እያንዳንዱን የግብፆች ዕርምጃ በጥንቃቄና በትኩረት መከታተል እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡
መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ በተለይ በዓባይ ጉዳይ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር በማድረግ፣ በመስኩ ዕውቀት ያላቸውን ባለሙያዎችና ምሁራን በማሳተፍ፣ በየደረጃው የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የአገሪቱን ግልጽ አቋም ማሳወቅ እንደሚኖርበት የሚጠይቁ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተለይም በዩኒቨርሲቲዎችና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ምሁራን በዚህ ብሔራዊ ጉዳይ ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ ሲገባቸው ብዙዎቹ ዝምታ መምረጣቸውንም ይተቻሉ፡፡
የአገሪቱ ሕዝብ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ የውጭና የአገር ውስጥ ሚዲያዎች የታላቁ ህዳሴ ግድብ በግብፅ ባለሥልጣናት ለምን ተቃውሞ እንደሚቀርብበት፣ የግድቡ ግንባታን የጥራት ደረጃና ሙሉ ምሥል የሚያሳይ መረጃ የማቅረብ ኃላፊነት የመንግሥት በመሆኑ ትኩረት እንዲደረግበት በአፅንኦት ያሳስባሉ፡፡ ሰሞኑን የግብፅ ባለሥልጣናት ሱዳንን ከኢትዮጵያ ለመነጠል የጀመሩትን ዘመቻና ተለዋዋጭ አቋማቸውን በተጨባጭ ማጋለጥ እንዲያስችለው ዘርፈ ብዙ ዝግጅት ለማድረግ ዜጎችን በምልዓት ማሳተፍ አለበት ሲሉ ያስረዳሉ፡፡